
“ሴቶች ከትምህርት ገበታ እንዳያቋርጡ በቅንጅት የሚሠራው ሥራ ውጤታማ እንዲኾን ጥረት ማድረግ ይገባል” የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ
ባሕር ዳር: መስከረም 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዞኑ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ የሮምነሽ ጋሻውጠና የሴቶችን የትምህርት ማቋረጥ፣ ጎጅ ልማዳዊ አስተሳሰብና ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ኀላፊዋ በዞን ደረጃ በምክትል አሥተዳዳሪ በሚመራ የጎጅ ልማድ አስወጋጅ ኮሚቴ አማካኝነት ተቋማት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡
ኮሚቴው በወረዳ ደረጃም መኖሩን የገለጹት ወይዘሮ የሮምነሽ ሲቪክ ማኅበራትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ለሴቶች የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ብሎም በኢኮኖሚ በመደገፍ ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ድጋፍ እያደረጉ ስለመኾኑ አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም በዞኑ ሴት ተማሪዎች በጎጅ ልማዳዊ አስተሳሰብና ድርጊቶች ተጽእኖና በሰላም እጦት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ከትምህርት ገበታ እየተለዩ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
ሴቶች ከትምህርት ገበታ እንዳያቋርጡ በቅንጅት እየተሠራ ቢኾንም ውጤቱ በቂ አይደለም ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ በተያዘው የትምህርት ዘመን የአቋራጭ ሴት ተማሪዎችን ቁጥር ለመቀነስ የሃይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ሲቪክ ማኅበራት ፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና አጋር አካላት ከተቋማቸው ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን በ2015 የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል 8 ሺህ 903 ሴቶች ከትምህርት ገበታ ማቋረጣቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!