
አርሶ አደሮችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር መጀመሩን አልማ አስታወቀ፡፡
የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ሞገስ እንደገለጹት በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ደረስጌ ማሪያም ቀበሌ ለዚሁ ተግባር 130 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ መረጃ ዘመናዊ መንደሩ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በጸሃይ ብርሃን እና በነፋስ 24 ሰዓት የሚሰራ የኃይል አቅርቦት፣ ትምህርት ቤት፣ የሰው እና የእንስሳት የህክምና መስጫ ተቋማት፣ መንገድ፣ የአርሶ አደሮች ማሰልጠ እና የኢንተርኔት አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች የሚሟሉለት ነው፡፡ ሥራው አሜሪካ ለአፍሪካ የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በልማት ለመቀየር ታስቦ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
ዘመናዊ መንደሮቹ የሙከራ ፕሮጀክት በመሆናቸው ለአርሶ አደሮች በነጻ እንደሚሰጡ የገለጹት አቶ አለማየሁ በቀጣይ ዘላቂነቱን ለማስጠበቅ ለሚሠሩ መንደሮች ግንባታ መንግስት፣ የፋይናስ ተቋማት እና አርሶ አደሮች እንዲሳተፉባቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡ የግንባታው ወጭም ሙሉ በሙሉ “ስማርት ቪሌጅ ሶሉሽን” በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ይሸፈናል፡፡ የሥራውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ለአርሶ አደሮች እስከ 40 ዓመታት የሚቆይ ተዘዋዋሪ ብድር ከግብረ ሰናይ ድርጅቱ እንደሚያቀርብም ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተበታተነ መልኩ የሚገኘውን የአርሶ አደሮች አሰፋፈር በአንድ ላይ በማሰባሰብ የመሠረተ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ መኖሪያ መንደሮቹ የአካባቢውን የቤት አሰራር በሚገልጽ መንገድ ከብረት እና ከእንጨት እንደሚገነቡም ነው አቶ ዓለማየሁ የተናገሩት፡፡ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር በኩል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖራቸውም ታምኗል፡፡ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚተገበር ነው፡፡ በደረስጌ ማሪያም ተጀምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚሰፋም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከቤቶች አስከ ቴክኖሎጅ ግንባታው ድረስ ያለው አጠቃላይ ሥራ እስከ ዘጠኝ ወራት ሊወስድ እንደሚችልም ነው አቶ አለማየሁ በተለይ ለአብመድ የገለጹት፡፡ በዚህ ወቅት የ130 ቤቶች የግንባታ ንድፍ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራ ንድፎች በሁለት ወራት ውስጥ ሲጠናቀቁ አጠቃላይ የግንባታው ወጭ ይፋ ይደረጋል፡፡ የመሬት አቅርቦቱን እና መሠረተ ልማት የማሟላቱን ኃላፊነት አልማን ወስዶ እየሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ቴክኖሎጅ የማቅረብ እና ግንባታውን የማከናወኑ ተግባር ደግሞ የ “ስማርት ቪሌጅ ሶሉሽን” ይሆናል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ