“በአማራ ክልል የወባ በሽታ ሥርጭት እና የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

54

ባሕር ዳር: መስከረም 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የወባ በሽታ ሥርጭት በቀጣይ በወረርሽኝ መልኩ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለበት ቢሮው አስታውቋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ እንደተናገሩት እስካሁን በክልሉ በወባ በሽታ ምክንያት የሚፈጠረው የሞት ምጣኔ አነስተኛ ቢኾንም ስርጭትና የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው። ክልሉ የወባ በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ተብሏል።

ቢሮ ኅላፊው ማኅበረሰቡም ለወባ በሽታ አጋላጭ የኾኑ ነገሮችን በመለየት እራስን መጠበቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የጤና ባለሙያዎችን ምክረ-ሃሳብ ማዳመጥና መተግበር ይገባል ያሉት አቶ አብዱልከሪም አካባቢ ማጽዳት፣ ቆሻሻን ማስወገድ፣ ያቆረ ውኃን ማፋሰስ፣ አጎበርን በአግባቡ እና ሁሌም መጠቀምን ባህል ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ የሕመም ምልክቶች ሲከሰቱ ቀድሞ ወደ ሕክምና ተቋም የመሄድ ልምዱ እንዳደገ መምጣቱን የተናገሩት ኀላፊው የጤና መድን ትግበራው ውጤት መኾኑን አንስተዋል። በክልሉ የጤና መድን አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት አባል ለመኾን ከሚፈቅድላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች 96 በመቶ መሸፈን ተችሏል ተብሏ።

የጤና መድን ኅብረተሰቡ ባዋጠው ገንዘብ በቀላሉ የሚታከምበት ሥርዓት ነው የሚሉት አቶ አብዱልከሪም ኅብረተሰቡ በሚያጋጥሙት ወረርሽኞች እና የጤና አደጋዎች ሁሉ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረግ አስችሏል ነው ያሉት። እንደ ኅላፊው ገለጻ መከላከልና ማከምን ማእከል ያደረገው የጤና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ትግበራ አበረታች ውጤትም አምጥቷል።

መንግሥት የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በትኩረት እየሰራ ነው ያሉት ኀላፊው የሃይማኖት አባቶችም ሕዝብን በማንቃት በወረርሽኝ መልኩ የሚከሰት በሽታ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመግታት ሚናቸው የላቀ ነውና ድጋፋቸውን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article231 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለ2016 የትምህርት ዘመን ዝግጁ መደረጋቸውን የደቡብ ወሎና አካባቢው አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
Next articleየትምህርት ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም የትምህርት ካላንደርን ይፋ አደረገ፡፡