ግድግዳቸው፣ ጣሪያቸው…አለት ነው፡፡ ድንቅ የኪነ ህንጻ አሻራ አርፎባቸዋል፤ ያያቸው ሁሉ ይደመማል፡፡

645

“ሂድ ሀገርህን ተመልከታት በዚች ምድር በመፈጠርህ እድለኛ መሆንህን ታይበታለህ፡፡” የኢትዮጵያ ባለውለታ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ

ሰው የሚያውቀው ክህነት የሌላቸው፤ ፈጣሪ የሚያውቀው ቅድስና አለ በልባቸው፡፡

ዘመኑ ግርማዊ ቀደማዊ ኃይለስላሴ በዙፋን ላይ የነበሩበት ወቅት ነው፡፡ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ልጅ አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን በአባታቸው አዛዢነት በእርሳቸው አስፈጻሚነት  እንደስማቸው ሁሉ ወሰን እያሰፉ ሀገር በፍቅርና በአብሮነት እንድትኖር ይታትሩ ነበር፡፡ አስፋው ወሰን ክብርና ልዕልና ከአባታቸው የወረሱ የተፈሩና የታፈሩ ነበሩ፡፡ በዙሪያቸውም ሲወጡና ሲገቡ እንደቅጠል እየረገፈ እጅ የሚነሳ አጋፋሪና አገልጋይ ነበራቸው፡፡ ሀሳባቸው የተቃና ስራቸውም የሰመረ እንዲሆን ቀን እና ለሊት በትጋትና በብስለት የሚያማክሯቸው እንደራሴዎችም ነበሯቸው፡፡

ፍርድ እንዳይጓደል፣ ደሃ እንዳይበደል እንደራሴያቸውን ያማክሩ ነበር፡፡ ከእነርሱ ጋር መክረው ዘክረው የእራሳቸውን ስልጣንም ተጠቅመው ፍርድ ይሰጣሉ፡፡ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን ምን አልባትም እርሳቸው ያላወቁት ቅዱሰነታቸውንም ያልተረዷቸው አንድ ታላቅ አባት እንደራሴ ሆነው ያገለግሏቸው ነበር፡፡ አኒያ አባት በጠላት ጊዜ አርበኛ፣ እንደራሴና ልባቸው ንጹህ የሆነ ታላቅ አባት ነበሩ፡፡ አርበኛ ናቸው ከጠላት ጋር ጉረሮ ለጉረሮ ተናንቀው የጠላትን አንገት አስደፍተዋል፡፡ ልዑል አልጋ ወራሹ ሕዝብ እንዳይበድሉ፣ ፍርድ እንዳያጓድሉ እንደራሴ ሆነው አማክረዋል፡፡

የአፍሪካ የጭቁንነት ቀንበር ሰባሪው የነጻነት ቀንዲል አብሳሪውና አብሪው ታላቁ ንጉስ የዳግማዊ ምኒልክ፣ የፈላስፋውና የጠቢቡ ሰው ዘርዓ ያዕቆብ እና የአያሌ ነገስታት፣ መኳንንት፣መሳፍንትና አርበኞች ሀገርም ናት፡፡ “በበልጅግ ሚግ” ከሰማይ ያወረደው የራስ አበበ አረጋይ እትብት የተቀበረባት ስፍራም ናት ሰሜን ሸዋ፡፡ ከዚህ ስፍራ በወንድነቱ ጠላትን አፈር የሚያስልስ፣ በእምነቱ አርአያ የሆነ ቅዱስ መወለድ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ከታሪካዊቷ ሰሜን ሸዋ ውስጥ ምንም ያልተወራለት እጹብ ድንቅ የሚያሰኝ ታሪክ ሞልቷል፡፡ ከደብረ-ብርሃን ከተማ በስተሰሜን ምስራቅ በሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ታላቅ ስፍራ እንቃኝ፡፡

አርበኛው፣ እንደራሴውና ቅዱሱ ሰው የሰሯቸውን ገዳማትም እንይ፤ ልዑል አልጋ ወራሽ ከመቃብር ተነስተው ይህን ድንቅ ነገር ቢያዩ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል አሰብኩትና ገረመኝ፡፡ የእርሳቸው እንደራሴ የነበሩ አርበኛና ጦረኛ ናቸው ብለው ሲያስቡ፣ መናኝና ጻዲቅ መሆናቸውን ሲያውቁ እራሳቸውን እንዴት ይታዘቡት ይሆን፡፡ የምንሄደው ከታላቁ ገዳም ኩክ የለሽ ማርያም ነው፡፡ በአንድ ስም ተጠራ እንጂ በውስጡ ተጨማሪ ሶስት ገደማት አሉ፡፡ ኩክ የለሽ  ማለት ጅሮው ውስጥ መስማትን የሚከለክል ነገር የሌለበት ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ማለት ነው ይላሉ፡፡

 

አካባቢው ወጣ ገባ የበዛበት በተፈጥሮ ድንቅ ጥበብ የታነጸ ነው፡፡ እስከ 1970ዎቹ መጀመሪያ ስፍራው የተቀደሰ እንደሆነ አንዳንድ አባቶች ቢናገሩም በውስጡ የታዬ ነገር አልነበረም፡፡ ገዳም ማለት ጫካ ዱር ምድረበዳ ተክል፣ ዘር እና ምግብ የሌለበት የጸሎት ቦታ ነው ይላሉ አበው፡፡በዚህ ቦታም መነኮሳት ጤዛ ለብሰው ድንጋይ ተንተርሰው ጽምጸ አራዊትን ታግሰው ይኖሩበታል፡፡

አባ ኃይለ ጊዮርጊስ መስከረም 23/1908 ዓ.ም በቡልጋ አውራጃ ነው የተወለዱት፡፡ ከመምህር ተቀምጠው በመማር ዲቁና ወይም ቅስና አልተቀበሉም፡፡ ይልቁንስ ጠመንጃ ይዘው አርበኛ ሆነው ጠላት ለመመከት ደፋ ቀና የሚሉ ነበሩ፡፡ እኒህ አባት የልዑል አልጋ ወራሽ አስፋው ወሰን እንደራሴና አማካሪም ነበሩ፡፡ ለልዑል አልጋ ወራሹ እና ለአብዛኛዎቹ ሰዎች አርበኛና ዓለማዊ ሰው ይመስሏቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን በንጹህ ልባቸው ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙ ሰው ነበሩ፡፡

በግራ ዕልፍ በቀኝ እልፍ በኋላ እልፍ በፊት እልፍ እየሆነ እንደቅጠል እየረገፈ የሚያጅባቸው አገልጋይና አሽከር የነበራቸው ግርማዊ ቀደማዊ ኃይለ ስላሴ ከአንድ ጎልማሳ እድሜ በላይ ከተቀመጡበት ዙፋን ወረዱ፡፡ ልጃቸው አልጋ ወራሽም እንዲሁ እጃቸው አጠረ፤ ተሰበሰበም፡፡ ያን ጊዜ ዓለም ምን ያክል አላፊ ጠፊ መሆኗን ልብ ይሏል፡፡ ጊዜ አንስቶ ጊዜ እንደሚጥልም ይረዳሉ፡፡ አባ ኃይለ ጊዮርጊስም ከእንደራሴነታቸው ለቅቀው በጾምና በጸሎት ተወስነው ለፈጣሪያቸው ይታዘዙ ጀመር፡፡ በሰሜን ሸዋ በሚገኙ አድባራትና ገዳማት እየተዘዋወሩ ጾምና ስግደት ያደርሱም ጀመር፡፡ መንፈሳዊነታቸው እየታወቀ የሄደውም ከ64 ዓመታቸው በኋላ ነበር፡፡  ድንቅ ነገር የተደረገላቸውም በጻድቃኔ ማርያም ሱባኤ ገብተው በነበረበት ጊዜ እንደነበርም ይነገራል፡፡ ከታሪካዊቷ ከተማ ደብረ ብርሃን በሰሜን መስራቅ ሰባት ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዙ ወደ ገዳሙ ከመውረድዎ  በፊት ከአፋፉ ላይ ሳርያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ይገኛል፡፡ በዚህ ቤተ ክርስቲያን አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ያገለግሉ ነበር፡፡ ብዙ ታምራትን እንዳዩበትም ይነገራል፡፡

እኝህ አባት በዚህ ቤተ ክርስቲያን በነበሩበት ወቅት ብዙ ሚስጥራትን አይተዋልም ሰርተዋልም ይባላል፡፡ ከቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ወደታች በሚገኘው ገደላማ ቦታም አብያተ ክርስቲያናትን ለመፈልፈል ፈቃድ ተሰጣቸው፡፡ ፈቃዱ ምድራዊ አይደለም፤ ሰማያዊ እንጂ፤ ዘላለማዊ እንጂ አላፊ ጠፊም አልነበረም፡፡  የኩክ የለሽ ማርያም ገዳም አስተዳደሪ መላዕከ ምህረት ፈቃደ ተክለጻዲቅ እንደነገሩን አባ ኃይለ ጊዮርጊስ በ1972 ዓ.ም የመጀመሪያውን ቤተ ክርስቲያን ከአለት ላይ መፈልፈል ጀመሩ፡፡ ቤተክርስቲያኑን እንዲሰሩ ፈቃድ የተሰጣቸው በጻድቃኔ ማርያም ውስጥ ሱባኤ በነበሩበት ጊዜ እንደነበር በህይወት ዘመናቸው ይናገሩ ነበር ብለውናል መላዕከ ምህረት ፈቃደ ፡፡ መጀመሪያ የሰሩት የቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የታነጸውም በ1972 ዓ.ም እስከ 1976ዓ.ም ባለው ጊዜ ነው፡፡ ይህን እንደጨረሱ ኩክ የለሽ ማርያም ፍልፍል ዋሻን መስራት ጀመሩ፡፡

በ1984ዓ.ም ጀምረው በአንድ ዓመት ውስጥ አጠናቀቁ፡፡ ኩክ የለሽ የተባለችውም የጀሮ ኩክ የሌላት፣ የጠየቋትን ቶሎ የምትሰማና መልስ የምትሰጥ በመሆኑ ነው ይላሉ አበው፡፡ በምሳሌ ሲያስረዱም አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ጥያቄያቸው በሚያምኗት ቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄያቸው ስለተሰማላቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሦስተኛው ዋሻ የቅድስት ስላሴ ፍልፍል ዋሻ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የተሠራውም ከኩክ የለሽ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በተመሳሳይ ዓመት ነው፡፡ አራተኛው ፍልፍል ዋሻ ምን ያምር ቅዱስ ገብርኤል ፍልፍል ዋሻ ነው፡፡ ምንያምር ቅዱስ ገብርኤል  የተሰራውም በ1986 ዓ.ም ነው፡፡ በምንያምር ቅዱስ ገበርኤል ቤተ መቅደስ ውስጥ ጸበል ፈልቆ ብዙ ታምራትን እንደሚያደርግም አበው ነግረውናል፡፡ አራቱ ፍልፍል ዋሻዎች በ1972 ዓ.ም ተጀምረው በ1986 ዓ.ም ተጠናቀቁ፡፡ በ1987 ዓ.ም ፍልፍል ዋሻዎቹ ተባርከው ቅዳሴ ቤታቸው ተከብሯል፡፡እኝህ ታላቅ አባት ገዳማቱን መሥርተው ብዙ መንፈሳዊ ተጋድሎ ካደረጉ በኋላ መጋቢት 19/1997 ዓ.ም በክብር አረፉ፡፡  በቀድሞው አርበኛ በኋላው ቅዱስ አባት የተሠሩት አብያተ ክርስቲያናት በየቀኑ ማዕጠንት ይታጠንባቸዋል በየወሩ ደግሞ ቅዳሴ ይቀደስባቸዋል፡፡

በዚህ አካባቢ በፈጣሪያቸው ፈቃድ  በአባ ኃይለ ጊዮርጊስ መስራችነት ቤተመቅደስ ከመፈልፈሉ አስቀድሞ የከበሮ ድምጽ፣የእጣን ሽታና ሌሎች ቅዱሳን የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ይሰሙ እንደነበር መላዕከ ምህረት ፈቃደ ነግረውኛል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ ወደታች ሲወርዱ እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያንን በስተቀኝ፣ በስተግራ በኩል ደግሞ ኩክ የለሽ ማርያምንና ቅድስት ስላሴን ጎን ለጎን ያገኛሉ፡፡ እነዚህን ገዳማት በቀኝና በግራ ተመልክተው ወደታች ሲወርዱ ምንያምር ቅዱስ ገብርኤልን ያገኛሉ፡፡ ቤተ መቅደሶቹ የየራሳቸው የአሠራር ቅርጽና ስርዓት አላቸው፡፡ ከአራቱ ፍልፍል ዋሻዎች የምንያምር ቅዱስ ገብርኤል ለዬት ያለ ነው፡፡ በውስጡ ጸበል ፈልቀቆበታል፡፡ ሰፊና የተለያዩ ለጸሎት ማድረሻ የሚሆኑ ክፍሎችም አሉት፡፡ ከአራቱ ዋሻዎች መካከል ለኩክ የለሽ ማርያም ተጨማሪ ዘመናዊ ቤተ ክርስቲያን ተሰርቶላታል፡ ሌሎቹ ግን አባ ኃይለ ጊዮርጊስ በሠሯቸው ቤተ መቅደሶች ብቻ ነው የሚገለገሉት፡፡ ወደዚህ ድንቅ ገዳም ውስጥ በየጊዜው ብዙ ቁጥር ያላቸው የኃይማኖቱ ተከታዮች እንደሚሄዱ አበው ነግረውናል፡፡ ገዳሙ የጎብኚ መዳረሻ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆንም መላዕከ ምህረት ፈቃደ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ትናንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ አለት ጠርበው ቤተመቅደስ ያንጻሉ፡፡ በፈጣሪያቸው ይመካሉ፣ ወገንና ባዕድ ሳይሉ ሰው የሆነውን ሁሉ ያከብራሉ ይወዳሉ፡፡ በሀገራቸውና በማንነታቸው የመጣውን ደግሞ አሳፍረው ይመልሳሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠላት ሲቆጣ በነፍጥ ፈጣሪ ሲቆጣ ደግሞ በጸሎትና በስግደት ማብረዱን ያውቁበታል፡፡ኢትዮጵያ ለዓለም ብዙ ነገርን አብርክታለች፡፡ የተሰራችበት መሠረት፣ የታነጸችበት ግድግዳ ሊመረመር አይችልም፡፡ እንደሌሎቹ ሁሉ ምድር ብትሆንም በርካታ ሚስጥራትንና ጥበብን የያዘች ስለሆነች ከምድር ትለያለች፡፡ ላፍርሳት ያለ አይሳካለትም፡፡ በክፉ ልያት ያለ አይኑ አያይለትም፡፡ ለምን ቢሉ በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም ዓለም ድንቅ የሆኑ ልጆች አሏትና ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያጥላሉ ጥቂቶች ናቸው፤ በውስጧ የሚጠለሉ ግን እልፍ አዕላፋት፡፡ ሂድ ከጫፍ አስከጫፍ ታሪኳን እይ! ትረካለህ፤ ጨለማ የሌለበት ተስፋም ታያለህ፡፡

ሂድ!  ሀገርህን ተመልከታት! በዚች ምድር በመፈጠርህ እድለኛ መሆንህን ታይበታለህ፡፡ ሰላም፡፡

በታርቆ ክንዴ

Previous articleበኩር ጥር 11-2012
Next articleበአማራ ክልል ሁሉንም መሠረተ ልማቶች ያሟላ የአርሶ አደሮች መንደር ሊገነባ ነው፡፡