
ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እድሚያቸው አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ ለኾኑ ሰዎች ከመስከረም 5 ጀምሮ እስከ መስከረም 10/2015 ዓ.ም የሚሰጠው የኮሌራ ክትባት ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንደተናገሩት በክልሉ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ዜሮ የማድረግ ዘመቻ ስኬታማ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት ያስፈልጋል።
በዓለም ጤና ድርጅት ብያኔ መሰረት አንድ ሰው ላይ ብቻም ቢኾን የኮሌራ ኬዝ ከተገኘ እንደ ወረርሽኝ የሚቆጠር ነው የሚሉት አቶ በላይ አሁን ላይ በአማራ ክልል በ28 ወረዳዎች ተከስቷል ብለዋል።
ከ3ሺህ 8መቶ በላይ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል፣ ከ70 በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል ነው ያሉት። በየቀኑ ከ15 እስከ 20 ሰዎች በአዲስ በበሽታው እየተጠቁ መኾኑን ሪፖርታችን ያመላክታል ነው ያሉት።
ለተከታታይ 10 ቀናት በዘመቻ በሚሰጠው የኮሌራ ክትባት ባሕር ዳርና ጎንደር ከተማን ጨምሮ 9 ወረዳዎች ላይ ክትባት ለመስጠት አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ ነው የተናገሩት። ለ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰዎች ክትባቱን ለመስጠት ታቅዷል ተብሏል። በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት፣አጋር አካላት፣የሃይማኖት አባቶች፣ወጣቶች የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ክትባቱ በታለመለት ዓላማ እንዲሰጥ ግንዛቤ በመፍጠርና በማስተባበር በኩል ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው ኮሌራ በሽታና ወረርሽኙ በአይነቱም በሚያስከትለውም ኩዳት አደገኛ ነው ብለዋል። በመኾኑም ኅብረተሰቡን ከአስከፊው በሽታ ለመታደግ ለሚሰጠው ክትባት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ስርጭቱን ለመግታት ቅንጅታዊ አሠራርን በመግባባትና በመናበብ መምራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እስካሁን ባለው ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል ለኅብረተሰቡ ግንዛቤና መረጃ በመስጠቱ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል። የኮሌራን ክትባት በዘመቻ ለመስጠት የተጀመረው ከፍተኛ የወረርሽኙ ስጋትና ችግር ያለባለባቸውን አካባቢዎች በማስቀደም ነው።
ከክትባቱ ባሻገርም የኮሌራ በሽታን መከላከል የሚያስችሉ መንገዶችን በትክክል መተግበር ይገባል ነው ያሉት።
በሃይማኖታዊ ጉዳይ በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡበትና በሌሎችም አካባቢዎች የንጽህና መጠበቂያን ማሟላት፣መጸዳጃ ቤቶችን ማዘጋጀት፣የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባም መክረዋል። የግልና የጋራ አካባቢን ጽዱና ውብ ማድረግ፣ ለተላላፊ በሽታ ተጋላጭ የሚያደርጉ ጉዳዮችን ሁሉ ማስወገድም እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
ለኅብረተሰብ ጤና መረጋገጥ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ክትባቱ የሚኖረውን ፋይዳ መረዳትና ማስረዳት፣ለስኬታማነቱም ኀላፊነትን መወጣት ተገቢ ነው ብለዋል። እድሚያቸው ከአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የኾናቸው ሰዎች ክትባቱ በሚሰጥባቸው የጤና ተቋማት በመሄድ የኮሌራ ክትባት እንዲወስዱም ቢሮ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!