
ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዛሬ መሰጠት የጀመረው የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት ስኬታማ እንዲሆን የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የክልሉ ጤና ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።
የኮሌራ መከላከያ ክትባት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በባሕር ዳር ተካሂዷል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ የኮሌራ በሽታ አደገኛ የማኅበረሰብ ጤና ችግር በመሆኑ ይህንን በመረዳት በሽታውን ለመቆጣጠር የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የብሔራዊ የኮሌራ ማስወገድ አስተባባሪ አቶ የሻምበል ወርቁ፣ በሽታው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በ11 ክልሎች ተስፋፍቶ ከ24 ሺህ በላይ ሰዎችን በማጥቃት የ320 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል ብለዋል።
እንደ ሀገር በሽታውን ለመቆጣጠር ከዓለም አቀፍ ተቋማት በተገኘ የ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን የክትባት ድጋፍ በተለያዩ ክልሎች ክትባቱ ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ገልጸው፣ አሁን ላይም በአማራ ክልል ክትባት መስጠት ማስፈለጉን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!