በሰሜን ወሎ ዞን 25 የግንባታ ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ለምረቃ ዝግጁ ማድረጉን የዞኑ አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

88

ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በክልሉ ማኅበራዊ ዘርፍ መሻሻሎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡ አልማ በአማራ ክልል ጥራት ያለው ትምህርት እና የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በየዓመቱ የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ይተገብራል፡፡

በአማራ ልማት ማኅበር የሰሜን ወሎና አካባቢው ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ካሳሁን አምባዬ አልማ በሰሜን ወሎ የማሕበራዊ ተቋማት ግንባታ ፕሮጀክት ትግበራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አልማ በትምህርት፣ በጤና እና በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ (በቴክንኒክና ሙያ ግንባታ) በትኩረት እየተሳተፈ ነው ብለዋል፡፡

በዞኑ ከ2014 ዓ.ም የዞሩ 27 በትምህርት፣ አንድ በጤና እና ሁለት የቴክኒክና ሙያ ያልተጠናቀቁ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በ2015 ዓ.ም ማስቀጠላቸውን አስታውሰዋል፡፡ በ2015 ዓ.ም ደግሞ 18 የትምህርት፣ 4 የጤና፣ 3 የቴክኒክና ሙያ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደ አዲስ መስራታቸውንም ገልጸዋል፡፡ አልማ በወረራው የተጎዳውን የጤና ዘርፍ በትኩረት እያገዘ መሆኑን ያነሱት ኅላፊው የክልሉ ጤና ቢሮ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ለአምቡላንስ መግዥያ የሚውል 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ማስተላለፋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በዞኑ 25 የግንባታ ፕሮጀክቶችን አጠናቀው ለምርቃ ዝግጅ ማድረጋቸውንም ያወሱት ኅላፊው በ2016 ዓ.ም ሁለተኛው እና ሦስተኛው ሩብ ዓመት የሚጠናቀቁ ሌሎች 25 የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ነግረውናል፡፡ አልማ ገንዝብ ከሕዝብ በማስተባበር እንደሚሰበስብ እና መልሶ ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን እንደሚገነባም ተጠቁሟል፡፡

የማኅበረሰብ ተሳትፎ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት አቶ ካሳሁን አልማ ከትምህርት ቤት ግንባታ ባሻገር በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ መጠለያ ጣብያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጊዜያዊ ትምህርት ቤት በድንኳን ከፍተው አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በክረምት ወቅት ከጃራ መጠለያ ጣብያ በተጨማሪ በጦርነቱ በተጎዱት ራያ እና ሃብሩ አካባቢዎች 51 መማሪያ ክፍሎችን በመክፈት ለበርካታ ተማሪዎች ትምህርት ተደራሽ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ክልሉን ማሳደግ ከተፈለገ ትምህርትን ቁጥር አንድ አጀንዳ አደርጎ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ኅላፊው አልማ ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አልማ የሚበጀተውን በርካታ በጀት ለትምህርት ተቋማት እንደሚውል መደረጉንም ነው የነገሩን፡፡

አልማ በሰሜን ወሎ ሁሉም ወረዳዎች የግንባታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ትልቁ የትኩረት ማዕከላቸው ትምህርት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በትምህርት ዘርፉ በርካታ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ የተናገሩት ኃላፊው ኀብረተሰቡ አልማን በመደገፍ የትምህርት ቤቶችን የጥራት ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመተጋገዝና በቅንጅት መሥራት ከተቻለ በታቀደው መሠረት የትምህርት ቤቶችን የጥራት ደረጃ ማሳካት ይቻላል ያሉት አቶ ካሳሁን በ2015 ዓ.ም ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን የመገናኛ አመራር ሰልጣኞች አስመረቀ።
Next articleየፌደራል ፖሊስ ተቋማዊ አቅሙ እና አሕጉራዊ እውቅናው እያደገ መሆኑን አስታወቀ።