“ከመስከረም እስከ ታሕሳስ ወባ በከፍተኛ ኹኔታ የሚተላለፍበት በመኾኑ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

79

👉በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ145 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታው ተጠቅተዋል።

ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እየተባባሰ በመጣው የወባ በሽታ ስርጭት ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ከ145 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል።
የፌዴራል መንግሥት እና ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች የርጭት ኬሚካል፣ መድሐኒት እና የምርመራ ግብዓት ድጋፍ እዲያደርጉም ኢንስቲትዩቱ ጠይቋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የወባ በሽታ ስርጭትና ሞት መጠን ከፍተኛ ቁጥርን የሚይዘው የአፍሪካ አሕጉር እንደኾነ የአፍሪካ አቀፍ የወባ ቁጥጥር ማኅበር እና የጤና ሚኒስቴር መስከረም 4/2016 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያም የፀጥታ እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮች ስርጭቱን ለመከላከል እንቅፋት መኾናቸው ተነስቷል።

ስርጭቱ በተለይ በአምራቹ ማኅበረሰብ ውስጥ እና በግብርና ሥራዎች ወቅት እየተከሰተ ትልቅ የኢኮኖሚ ችግር እንደፈጠረም ተገልጿል። የጤና አገልግሎት ተደራሽ በኾነባቸው አካባቢዎችም ጭምር የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ክፍተቶችም መኖራቸው ለችግሩ አባባሽ ምክንያት ኾኗል ነው የተባለው።

በአማራ ክልል ባለፉት ሦስት ዓመታት የወባ በሽታ ስርጭቱ መጨመሩን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ ኀላፊ በላይ በዛብህ እንዳሉት በ2014 በጀት ዓመት 1 ሚሊዮን ለሚኾኑ የወባ ሕሙማን ሕክምና መሠጠቱን በማሳያነት አንስተዋል። ከሐምሌ 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የወባ ተጠቂዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በሁለት ወራት ብቻ ከ145 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውን ነው የገለጹልን።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው የኬሚካል እጥረት ከስድስት ወረዳዎች ውጭ ርጭት አለመካሄዱንም አቶ በላይ ተናግረዋል። በክልሉ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የወባ መድሃኒት እና የምርመራ ኪቶችን የማቅረብ ችግር ስለመግጠሙም አንስተዋል።

ከመስከረም እስከ ታሕሳስ መጨረሻ ያለው ጊዜ ወባ በከፍተኛ ኹኔታ የሚተላለፍበት ወቅት መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ፤ ሥርጭቱን ለመቀነስ መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የአልጋ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የቁጥጥር ሥራ መሥራት፣ እንደ ትኩሳት፣ ማንቀጥቀጥ፣ ብርድ ብርድ ማለት እና ራስ ምታት የመሳሰሉ ምልክቶች ሲታዩ ደግሞ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ ክትትል ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡የጤና ባለሙያዎችም ስለ በሽታው ኹኔታ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም በመፈጠሩ የፌደራል የመድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ግብዓት እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል። የፌደራል መንግሥት እና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችም የጤና ግብዓቶችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሳውዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
Next articleየኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን የመገናኛ አመራር ሰልጣኞች አስመረቀ።