ፍቅረማርያም ያደሳ በኦሊምፒክ ቦክስ ማጣሪያ ሁለተኛ ኾኖ አጠናቀቀ።

75

ባሕር ዳር: መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሴኔጋል ዳካር በተካሄደው የአፍሪካ ዞን የኦሊምፒክ ቦክስ ስፖርት ማጣሪያ ውድድር በ57 ኪሎ ግራም ፍቅረማሪያም ያደሳ ሁለተኛ ኾኖ አጠናቋል።

ከናይጄሪያው ጆሽዋ ኦሞሌ ጋር የሦስት ዙር ፍልሚያ ቢያደርግም 3ለ2 በኾነ ውጤት ተሸንፎ ከፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ ውጪ ኾኗል።

ፍቅረማርያም (ጊችሮ ነብሮ) በጀግንነት በተፋለመባቸው የመጨረሻው ውድድር ውጤት ባይቀናውም እስከ ፍጻሜ ተፋላሚነት ድንቅ ብቃት ማሳየት ችሏል።

ለዛሬው የፍጻሜ ፍልሚያም የበቃው የአራት ሀገራት የቦክስ ተወዳዳሪዎችን አሸንፎ ነው። ይህም በመጀመሪያው ውድድር የኬኒያውን ተወዳዳሪ በአንደኛው ዙር በዝረራ በማሸነፍ ነው። በሁለተኛው ግጥሚያ የሊቢያውን ተወዳዳሪ ፣ በ2ተኛ ዙር በዳኛ ውሳኔ፣ በሦስተኛው ፍልሚያ የሞዛንቢክን ተወዳዳሪ በነጥብና በአራተኛው ውድድር የአልጄሪያውን ተወዳዳሪ በነጥብ 5 ለ 0 በኾነ ውጤት በማሸነፍ ነበር።

በሴኔጋል ዳካር ከጳግሜ 4 እስከ መስከረም 4 ድረስ በተካሄደው የአፍሪካ ሀገራት የኦሊምፒክ የቦክስ የማጣሪያ ውድድር 41 ሀገራት ተሳታፊ ናቸው። በመድረኩም 235 ቦክሰኞች መሳተፍ ችለዋል፡፡

እንደ ኢፕድ ዘገባ ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ላይ በአራት ወንድና ሁለት በሴት በድምሩ ስድስት ቦክሰኞችን ማሳተፍ ችላለች።

ኢትዮጵያ ከ1952 ጀምሮ በኦሊምፒክ የቦክስ ውድድር ለመሳተፍ በአስመራና አዲስ አበባ ትልቅ እንቅስቃሴ የተደረገ ቢኾንም ብሔራዊ ፌዴሬሽን ገና ስላልተቋቋመ መሳተፍ አልቻለችም። በ1964 ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎ ማድረግ ችላለች። ከዚያ በኋላም 1968 ሜክሲኮ፣1972 ሙኒክ፣ 1980 ሞስኮ፣ 1992 ባርሴሎና፣ 1996 አትላንታ፣2000 ሲድኒ፣2004 አቴንስ፣2008 ቤጂንግ ኦሊምፒኮች መሳተፍ ችላለች።

ለመጨረሻ ጊዜ በተሳተፈችበት የቤጂንግ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ውድድሩ ያቀናው የቦክስ ተፋላሚ ክብደት በመጨመሩ መፋለም እንዳልቻለ አይዘነጋም።

ከለንደን፣ሪዮና ቶኪዮ በኋላ በኦሊምፒክ ተሳታፊ ለመኾን ጫፍ የደረሰው የሦስት ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ፍቅረማርያም ያደሳ ሴኔጋል ላይ ባሳየው ድንቅ ብቃት ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢኾንም መጨረሻ ላይ ሊሳካለት አልቻለም።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሉሲዎቹ ከቡሩንዲ ጋር የሚያደረጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል” የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
Next articleየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሳውዲ አረቢያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።