
ባሕርዳር፡ መስከረም 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አራተኛው የዓባይ ግድብ የውኃ ሙሌት ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የደህንነት ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የዓባይ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የዓመቱ አንዱና ትልቁ ስኬት ማሳያ ነው፡፡
እንደ ሀገር መተባበር በጉልህ የታየበት፣ ውጤታማነቱ ያደገበት፤ በግድቡ ላይ እስካሁን የነበሩትን የዲፕሎማሲ ጫናዎች ተቋቁሞ አሁን ላይ የደረሰበት ትልቅ ሀገራዊ ስኬት የተገኘበት ነውም ብለዋል፡፡
አራተኛው የዓባይ ግድብ ሙሌት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት በመሆኑ ኢትዮጵያ ልትኮራበት የሚገባው ጉዳይ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ሌሎችም ይህንን ተገንዝበው የዓባይ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር የተፋሰሱን ሀገራት እንደሚጠቅም ከግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው ነው የገለጹት፡፡
የግድቡ ሥራ ከተባበርንና አንድ ከሆንን እንዲሁም ለአንድ ዓላማ ቆመን ከሠራን የማይሳካ ነገር እንደሌለ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ የመስራት አቅም እንዳለንና ችሎታው ደግሞ የተሻለ ሁኔታ መፍጠር እንደሚችል በዓባይ ግድብ ሥራ መታየቱንም አመልክተዋል፡፡
ኢንጂነሮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎች ባለፉት በርካታ ዓመታት የሠሩት ሥራ ግድቡ ሙያዊ አቅምን ከመፍጠር አንጻር ትልቅ ትምህርት የሰጠ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በግድቡ ሥራ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያዊያን በስፍራው በመዋልና በማደር ሙያቸውን በሚገባ በተግባር ያሳዩበት ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ ይህ ከኢትዮጵያም አልፎ ለሌሎች ሀገራትም ትምህርት ሊሆን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ዲና እንዳሉት፤ ባሳለፍነው 2015 ዓ.ም በርካታ ተግዳሮቶች የመኖራቸውን ያህል በዲፕሎማሲው መስክ አመርቂ ውጤቶች ተመዝገበዋል፡፡ በዋናነት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረውን ጦርነት በሠላማዊ መንገድ ለመቋጨት የተደረጉት እንቅስቃሴዎችና በመጨረሻም ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ውጤት ነበር፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ከተለያዩ አካላት ይደርሱ የነበሩ ጫናዎችን ለመቋቋም የተደረጉ ጥረቶች ከሞላ ጎዳል ስኬታማ እንደነበሩም አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል፡፡ ጫናው እያለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መታየቱንም አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነትም ትልቁ የዲፕሎማሲ ስኬት መሆኑን በመግለጽ፤ ይህም የዲፕሎማሲውን ምህዳር እንደሚያሰፋ፤ ተጨማሪ ወዳጆችን በተለየ መልክ ለመፍጠር እድል እንደሚሰጥ፤ ንግድና ኢንቨስትመንትን እንደሚሳለጥ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንደሚያፋጥን እና በአጠቃላይ የዲፕሎማሲና ፖለቲካ መደጋገፍን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ኢፕድ እንደዘገበው በዓመቱ ኢትዮጵያ በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ያደረገችው ተሳትፎ ጥቅሟን ሊያራምዱ የሚችሉ አቋሞች የተንጸበራቁበት እንደመሆናቸው በመስኩ ትልቅ ውጤት መገኘቱንም አስታውቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!