በአዲስ አበባ እና ጋምቤላ ክልል ለሚካሄዱ የአጀንዳ ልየታ መድረኮች ተወካዮችን የመለየት ሥራ ሊጀመር መኾኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።

41

አዲስ አበባ: መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአዲስ አበባ እና ጋምቤላ ክልል ለሚካሄዱ የአጀንዳ ልየታ መድረኮች ተወካዮችን የመለየት ሥራ ሊጀመር መኾኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከመሥከረም 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በ11 ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 119 ወረዳዎች ውስጥ ተወካዮች ይለያሉ ብለዋል። የተወካዮች ልየታ በሁለት ዙሮች እንደሚካሄድ ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር 60 ያህል ወረዳዎች ይሳተፋሉ። ሁለተኛው ዙር ደግሞ መሥከረም 12/2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲኾን ቀሪዎቹ ወረዳዎች በዚሁ ዕለት ይሳተፋሉ ተብሏል። ከእያንዳንዱ ማኅበረሰብ 2 ተወካዮች እንዲመረጡ በማድረግ ከየወረዳው በአማካይ 16-18 የሚኾኑ ተወካዮች ይመረጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በዚህ መሰረት ከ1 ሺህ 900 እስከ 2 ሺህ 140 ተወካዮች በአጀንዳ ልየታ መድረኩ ይሳተፋሉ ተብሏል።

በጋምቤላ ክልልም በ14 ወረዳዎች ከመሥከረም 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ልየታ መድረክ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ሥራው የተሳካ እንዲኾን ኅብረተሰቡ በንቃትና በቅንነት እንዲሳተፍ ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- በለጠ ታረቀኝ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ለሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር የተለያዩ ተቋማት የመሪዎች ሹመት ሰጠ።
Next article“አራተኛው የዓባይ ግድብ ሙሌት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ