“አልማ ያስገነባቸው 284 የመማሪያ ክፍሎች ለትምህርት ዘመኑ ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል” የጎንደር አካባቢ አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት

49

ባሕርዳር፡ መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ያስገነባቸው 284 የመማሪያ ክፍሎች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የጎንደር አካባቢ አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለኸኝ ጓዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመማሪያ ክፍል ጥበት ችግር ለመፍታት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

ማኅበሩ በጎንደር ከተማ፣ በሰሜን፣ በማዕከላዊ እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በሚገኙ 71 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ላስገነባቸው የመማሪያ ክፍሎች 286 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ከመማሪያ ክፍሎቹ በተጨማሪ 5 ቤተ-መጻህፍት እና ሁለት የተማሪዎች መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን አቶ አለኸኝ ተናግረዋል።

የመማሪያ ክፍሎቹ ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ያላቸው ሲሆን በአዲሱ የትምህርት ዘመን የነበረውን የክፍል ጥበት እንደሚያቃልሉ አመልክተዋል።

የመማሪያ ክፍሎቹ ግንባታ መንግስት በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የጀመረውን የትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል ንቅናቄ ያግዛል ብለዋል።

ለትምህርት ተቋማቱ ግንባታ ማህበረሰቡ በጥሬ ገንዘብ፣ የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ እና በጉልበት 236 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

ልማት ማኅበሩ በዞኖቹ በ55 ሚሊዮን ብር ወጪ እያስገነባቸው የሚገኙ 43 የትምህርት ፕሮጀክቶች እንዳሉም አቶ አለኸኝ ገልጸዋል።

“ለአዲሱ የትምህርት ዘመን በሰባት ትምህርት ቤቶች 42 የመማሪያ ክፍሎችን የያዙ 10 ሕንጻዎች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ከተማ አልማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ናቸው።

በተጨማሪም በ15 ትምህርት ቤቶች 19 የመማሪያ ክፍሎችና የቤተ መጻህፍት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፈው ዓመትም 99 የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስታውሰዋል።

“በጎንደር ከተማ የትምህርት መሰረተ ልማት ያልተሟሉላቸው 69 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ” ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ውበት ናቸው።

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ሕዝባዊ ንቅናቄ አልማ በትምህርት ቤቶች ተጨማሪ የመማሪያ ህንጻዎችንና ቤተ-መጻህፍቶችን በመገንባት ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።

“አልማ የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የመማሪያ ክፍሎች በመገንባት እያገዘን ነው” ያሉት ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጭልጋ ወረዳ ነዋሪ አቶ ፈንታሁን ካሴ ናቸው።

በማዕከለዊ ጎንደር ዞን የአለፋ ወረዳ ነዋሪ አቶ መንግስቴ ዋለ በበኩላቸው አልማ በአካባቢያቸው የሚያደርገውን የልማት ተሳትፎ ለማገዝ አባል በመሆን በየዓመቱ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ እየከፈሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዓባይ ግድብ ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን ቁጥር 7 ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ገለጸ።
Next articleየአማራ ክልል መንግሥት ለደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር ለ20 መሪዎች ሹመት ተሰጠ፡፡