በዓባይ ግድብ ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን ቁጥር 7 ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ገለጸ።

46

ባሕርዳር፡ መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዓባይ ግድብ ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን ቁጥር 7 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር/ኢንጅነር) ገልጸዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም ሃይል ማመንጨት ከጀመሩት ሁለት ተርባይኖች በተጨማሪ በያዝነው 2016 በጀት ዓመት 5 ተርባይኖችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው፡፡ 5ቱ ተርባይኖች ወደ ስራ ሲገቡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያላትን 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት የሃይል አቅርቦት መጠን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል ፡፡

ወደ ስራ ከገቡት ሁለት ተርባይኖች አንጻር ዘንድሮ ወደ ስራ የሚገቡት 5ቱ ተርባይኖች ሃይል መጠን የበለስ ፣የግልገል ጊቤ አንድና ሁለት እንዲሁም የተከዜ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከሚሰጧቸው አማካይ 1 ሺህ 180 ሜጋ ዋት ተመጣጣኝ ወይም የሚበልጥ ሃይልን ያመነጫሉ ብለዋል።

ይሁንና ከአቀማመጡና ከውሃ ፍሰቱ አኳያ የእነዚህን አምስቱ የሃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሃይል የማመንጨት አቅም አሁን ላይ ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በ13ቱ ተርባይኖች 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይልን ወደ ብሄራዊ የሃይል ቋት እንደሚቀላቀልም ነው ሚኒስተሩ የገለጹት፡፡ በዚህም እያንዳንዳቸው ተርባይኖች በአማካይ ከ375 በላይ ሜጋ ዋት ሃይልን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች የኮሌራ ክትባት መቅረቡን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
Next article“አልማ ያስገነባቸው 284 የመማሪያ ክፍሎች ለትምህርት ዘመኑ ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል” የጎንደር አካባቢ አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት