
ባሕርዳር፡ መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ክትባቱ መስከረም 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ባለፈው ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልልም ከሐምሌ 7/2015 ዓ.ም ጀምሮ በቋራ ወረዳ ተከስቶ አሁን ላይ 28 ወረዳዎችን ማዳረሱን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኀላፊ በላይ በዛብህ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 11 ወረዳዎች ላይ በስፋት ተከስቷል ብለዋል፡፡ እስከ መስከረም 3/2016 ዓ.ም በክልሉ 3 ሺህ 820 ሰዎች በኮሌራ ተጠቅተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 2 ሺህ የሚኾኑት በቋራ ወረዳ የሚገኙ ናቸው። እስከ አሁን 78 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉን ነው ኀላፊው የገለጹት፡፡
በሽታውን ለመከላከል ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ፣ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመቀናጀት በተሠራው ሥራ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎችን መከተብ የሚያስችል ክትባት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ክትባቱ ከመስከረም 5/2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ክትባቱን ከመስጠት በተጓዳኝ የግልና የአካባቢ ንጽሕናን ፣ የመጠጥ ውኃ እና የምግብ ንጽሕናን በመጠበቅ በሽታውን የመከላከል ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የበሽታው ምልክት ሲከሰት ደግሞ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ ክትትል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በሽታውን ለመከላከል በሚሠራው ሥራ ማኅበረሰቡ በተለይም ደግሞ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!