“በዓለም ደረጃ በወባ በሽታ ስርጭትና ሞት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የአፍሪካ አህጉር ነው” አፍሪካ አቀፍ የወባ ቁጥጥር ማኅበርና ጤና ሚኒስቴር

68

አዲስ አበባ: መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የወባ በሽታ ስርጭትና ሞት መጠን ከፍተኛ ቁጥር ያለው በአፍሪካ አህጉር እንደኾነ የአፍሪካ አቀፍ የወባ ቁጥጥር ማኅበር እና የጤና ሚኒስቴር በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

መግለጫውን የሰጡት በጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተገኔ ረጋሳ (ዶ.ር) እና የአፍሪካ አቀፍ የወባ ቁጥጥር ማኅበር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው ካንትሪን ናቸው፡፡

በዓለም ካለው የወባ ስርጭት 95 በመቶ እንዲሁም ከሞት መጠኑ 96 በመቶ የሚኾነው በአፍሪካ አህጉር መኾኑን በመግለጫቸው አንስተዋል። ከፍተኛውን የወባ በሽታ ችግር የሚያስተናግደው አህጉር ችግሩን ለመቋቋም የሀገራቱን የጋራ የትብብር ተግባር በመጠየቁ የአፍሪካ አቀፍ የወባ ቁጥጥር ማኅበር ተመስርቶ ዓመታዊ ጉባኤውን ለማካሄድ ዝግጅት ላይ ነው ተብሏል።

የወባ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ያለውን ስርጭት ለመከላከል በነበረው ተግባር የፀጥታ ጉዳዮችና የአየር ንብረት ለውጥን የመሰሉ ችግሮች እንቅፋት ስለመኾናቸው አስረድተዋል።

ስርጭቱ በተለይ በአምራች ማኅበረሰቡና በግብርና ሥራዎች ወቅት እየተከሰተ ትልቅ የኢኮኖሚ ችግር እንደፈጠረም ተገልጿል። ከዚህ ባሻገር የጤና ተግባራቱ ተደራሽ በኾኑባቸው አካባቢዎች የማኅበረሰቡ የአጠቃቀም ክፍተቶችም ለችግሩ አባባሽ ምክንያት ኾኗል ነው የተባለው።

ከመስከረም 6 እስከ 10/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው በዚህ ዓመታዊ ጉባኤ ላይም የችግሩ አሳሳቢነትና አሁን ያለበት ኹኔታ እንዲሁም ያለፈውን ተግባር በመገምገም የቀጣዩ ተግባር ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
መድረኩም ለ9ኛ ጊዜ የሚካሄድ እንደኾነ ነው በመግለጫው የተገለጸው።

ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቶ ጎሹ እንዳላማው ወንድምአገኝ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኾነው ተሾሙ።
Next articleአዲሱ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ልዩ ልዩ ሹመቶችን ሰጡ።