አቶ ጎሹ እንዳላማው ወንድምአገኝ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኾነው ተሾሙ።

70

ባሕርዳር፡ መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ምክር ቤት በ4ኛ ዙር ምርጫ ፣11ኛ ዓመት፣ 9ኛ አስቸኳይ ጉባኤው አቶ ጎሹ እንዳላማው ወንድምአገኝን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሹሟል።

አቶ ጎሹ እንዳላማው በወረዳና በክልል በባለሙያነትና በተቋም ዳይሬክተርነት፣ እንዲሁም በዞንና በክልል አመራርነት አገልግለዋል።

በትምህርት ዝግጅታቸውም በክልልና አካባቢ ልማት ጥናት የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው ተገልጿል።

አዲሱ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባደረጉት ንግግር፤ ሕዝባችን ከገጠመው የሰላም እጦትና ቀውስ ለማውጣት በሰከነ ውይይትና ንግግር ለሰላም ተባብረን እንሠራለን ብለዋል።

በውቢቷ ከተማ ባሕር ዳር ሰላመዊ እንቅስቃሴ እንዲረጋገጥ በትጋት እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት።

ባሕር ዳር ከተማ ተፈጥሮ ያደላትን ጸጋ በመጠቀም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የነዋሪዎቿን ምቾትና ፍላጎት ለማሟላት እንሠራለን ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ፣ ዜጎችን የሚያማርሩ የመልካም አሥተዳደርና የልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች ተጋግዞ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠሩም አስገንዝበዋል።

በተፈጠረው ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ችግር ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል ብለዋል። በአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ልዩነት ያለው አይኖርም ያሉት አቶ ጎሹ፤ ልዩነቱ የሚኖረው በመፍቻ መንገዱ ላይ ነው ይላሉ።

እርስ በርስ በመጠፋፋት፣ ኢኮኖሚን በማውደም የሚመለስ ጥያቄ የለም ያሉት አቶ ጎሹ፤ በሰከነ መንገድ በውይይትና ንግግር ችግሮችን መፍታት አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

እናገለግለዋልን ለምንለው ሕዝብም ማኅበራዊ እረፍት ልንሰጠው ይገባልም ብለዋል።

ከተማዋ ከገጠመው የሰላም አለመረጋጋት ወደ አስተማማኝ ሰለሟ እንድትመለስ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ሕግና ስርዓት እንዲከበር ነዋሪዎቿም በሰላም እንዲኖሩ፣ ስርቆት ማጭበርበር፣ ብልሹ አሠራርና ሌሎችንም ሕገወጥ ድርጊቶችን እንዋጋለን ነው ያሉት።

በከተመዋ ከቀበሌ እስከ ክፍለ ከተማ ያለውን ውስብስብ አገልጎሎት አሰጣጥ ችግር፣ የመልካም አሥተዳደር ችግር ብልሹ አሠራርና ሌሎችንም ሕገወጥ ድርጊቶችንና ሌሎችንም ችግሮች ለመፍታት በቅንጅት እንደሚሠሩ የተናገሩት አቶ ጎሹ ሁሉም ከጎናቸው እንዲኾኑም ጥሪ አቅርበዋል።

የምክር ቤት አባላትም አዲሱ ካቢኔ በከተማዋ የሚታየውን ከፍተኛ የመልካም አሥተዳደርና ልማት ፣የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ ብልሹ አሠራር፣ የሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ ችግርሮች ፣የሰላምና የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየውኃ ወለድ በሽታዎችን በቅንጅት መከላከል እንደሚገባ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ገለጹ።
Next article“በዓለም ደረጃ በወባ በሽታ ስርጭትና ሞት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የአፍሪካ አህጉር ነው” አፍሪካ አቀፍ የወባ ቁጥጥር ማኅበርና ጤና ሚኒስቴር