
ባሕርዳር፡ መስከረም 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን በግብርናው ዘርፍ የሀገርን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ በተሠራው ሥራ ከሰብል ምርት 393 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በበጀት ዓመቱ ስምንት ነጥብ 69 ቢሊዮን ሊትር ወተት፣ 19 ሚሊዮን ቆዳና ሌጦ፣ 761 ነጥብ አምሥት ሺህ ቶን ቡና፣ 491 ነጥብ 35 ሺህ ቶን ሥጋ፣ 194 ነጥብ 27 ሺህ ቶን ማር፣ 101 ነጥብ አራት ሺህ ቶን የዓሣ ምርት መገኘት መቻሉንም ተገልጿል።
የግብርና ሚኒስቴር በማኅበራዊ የትስስር ገጹ እንደገለጸው፤ በ2014/15 ዓ.ም የምርት ዘመን በግብርናው ዘርፍ የሀገርን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የተሠራው ሥራ አበረታች አፈፃፀም ማሳየት ችሏል። አፈፃፀሙ እንደሚያሳየውም የሰብል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በአነስተኛ አርሶ አደሮች 13 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከ14 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ለምቷል። ከዚህም 393 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል።
በምርት ዘመኑ 761 ነጥብ አምሥት ሺህ ቶን ቡና፣ ስምንት ነጥብ 69 ቢሊዮን ሊትር የግመል፣ የበግ፣ የፍየልና የላም ወተት፣ 491 ነጥብ 35 ሺህ ቶን የዳልጋ ከብት፣ የበግ፣ የፍየልና የግመል ስጋ፣ 19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ቆዳና ሌጦ፣ 96 ሺህ ቶን የዶሮ ስጋ፣ ሦስት ነጥብ 918 ቢሊዮን እንቁላልና 194 ነጥብ 27 ሺህ ቶን የማር ምርት መገኘቱን በመረጃው ተብራርቷል።
የአነስተኛ አርሶ አደሮች የሆርቲካልቸር ሰብል 452 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ 656 ነጥብ 27 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 118 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተመርቷል፤ የዋና ዋና ሰብል ምርትን በሄክታር 31 ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 30 ኩንታል በሄክታር ማሳካት እንደተቻለ በማኅበራዊ ድረ ገጹ አስነብቧል።
በምርት ዘመኑ በኩታ ገጠም ስድሰት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማትና አራት ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ለማሳተፍ ታቅዶ በተሠራው ሥራ ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን፤ ስድስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬትም ለምቷል ተብሏል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማኅበራዊ በድረ ገጹ አያይዙ እንደገለጸው፤ በ2015 ዓ.ም የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ከሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ በሠራው ሥራ፤ ከ2 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት ታርሶ አብዛኛው ክፍል በበቆሎ፣ በገብስ፣ በማሽላና በሌሎች ምርቶች መሸፈን ተችሏል ሲል በድረ ገጹ አጋርቷል።
የበልግ እርሻ እንቅስቃሴውም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች መሠራቱን በመግለጽ፤ በሰብል ዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 65 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!