
ባሕር ዳር: መስከረም 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በተያዘው ዓመት ሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለተመደቡበት የትኩረት መስክና ተልዕኮ የዝግጅት ሥራ ቅድሚያ የሚሰጡ መኾኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኤባ ሚጀና እንደገለጹት፤ በ10 ዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ትኩረት መስክና ተልዕኮ እንዲሸጋገሩ የትግበራ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ተጀምሯል።
የትምህርት ሚኒስቴር የዘርፉን ስብራቶች ለማስተካከል ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን በትኩረት መስክና በተልዕኮ ተለይተው እንዲሠሩ ማድረግ ነው።
ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች በጥናት ላይ ተመስርቶ የምርምር፣ የተግባር፣ የአጠቃላይ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የትምህርት በሚሉ አምስት ዘርፎች ተደልድለዋል።
እንደ ሀገር ያለውን ነባራዊ ኹኔታ በመገምገምና የዓለምን ነባራዊ ኹኔታ ታሳቢ በማድረግ ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት መስክ ስለመመደባቸውም ነው ያነሱት።
ይህንን ለማስፈጸም የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ባለፈው ዓመት ለዩኒቨርሲቲዎች መላኩን ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲዎቹን ምደባ ለማከናወንም ያላቸው የመምህራን ብዛትና አቅም፣ የቤተ ሙከራዎች ብዛት፣ መሰረተ ልማት፣ ከኢንዱስትሪ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ጥናት ተደርጎ መኾኑን ዶክተር ኤባ ገልጸዋል።
የፍኖተ ካርታው ትግበራ በሦስት ምዕራፎች መከፈሉን አንስተው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ፤ ዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሮግራሞቻቸውን የመለየትና ከትኩረት መስካቸው ጋር የመከለስ፣ የአሠራር ሕግጋት ማውጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ከትኩረት መስካቸውና ከተልዕኳቸው አኳያ ወደ ሙሉ ትግበራ የሚያስገቡ መሰረተ ልማቶችን የማደራጀት ሥራ እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።
አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ ናቸው ያሉት ዶክተር ኤባ፤ አንዳንዶች የሕግ ሌሎች ደግሞ የትምህርት ፕሮግራም ክለሳ ላይ ናቸው ብለዋል።
ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ቅድሚያ ለተልዕኮና ለትኩረት መስካቸው እንዲሰጡ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው በዚህ ሂደት ውስጥ ያልገባ የትምህርት ተቋም ካለም ማስተካከያ ይደረግበታል ነው ያሉት።
በ2016 ዓ.ም የትኛውም የትምህርት ተቋም አዲስ የትምህርት ፕሮግራም እንደማይከፍት ገልጸው፤ በሌላ በኩል ይህ የትምህርት መስክ ይዘጋ ተብሎ የተወሰነበት የትምህርት ዓይነት አለመኖሩንም ተናግረዋል።
ኾኖም ተማሪዎች ሲመደቡ የማይፈልጉት የትምህርት ፕሮግራም ካለ ሊታጠፍ እንደሚችል ያነሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ “ይህ ማለት ግን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አይሰጥም ማለት አይደለም” ብለዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የዩኒቨርሲቲዎች የተማሪ ቅበላም በአብዛኛው ከትኩረት መስክ ጋር የተናበበ የሚደረግ ሲሆን በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች በየደረጃው ወደ ተመደቡበት የተልዕኮ መስክ የሚሸጋገሩ ይሆናል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!