“ግድቡ የኢትዮጵያ መጻዒ እጣ ፋንታ ተምሳሌት፤ የተፋሰሱ ሀገራት ጥምረት ማሳያ ነው” ሎውረንስ ፍሪማን

50

ባሕር ዳር: መስከረም 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ሁለት ታላላቅ ድሎችን እና እድሎችን የተጎናጸፈችው ኢትዮጵያ በፈተና መካከል በጽናት የማለፍ ተምሳሌት ኾናለች፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ሳምንታት ያገኘቻቸው ሁለት ታላላቅ ስኬቶች የሀገሪቱን መጻዒ እጣ ፋንታ በበጎ ጎኑ የሚተልሙ ናቸውም ተብሏል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ጆኦ-ፖለቲካል እና ፖለቲካል ኢኮኖሚ እሳቤዎች ላይ የላቀ ግንዛቤ ካላቸው የኢትዮጵያ ወዳጆች መካከል ዕውቁ አሜሪካዊ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ሎውረንስ ፍሪማን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአፍሪካ አህጉር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በጥምረት እና በትብብር የሚመጣ ነው የሚል ጽኑ አቋም ያላቸው ሚስተር ፍሪማን ኢትዮጵያ ለምታራምደው የትብብር እና አብሮ የማደግ እሳቤ ደጋፊ እንደኾኑም ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ሁለት ታላላቅ ድሎችን እና እድሎችን አሳክታለች የሚሉት ሎውረንስ ፍሪማን የታላቁ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጠናቀቅ ለኢትዮጵያዊያን የአዲስ ዓመት ገጸ-በረከት ነው ይላሉ፡፡ እንደ ምዕራባዊያኑ አቆጣጠር ከነሐሴ 22-24/2023 በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደው 15ኛው የብሪክስ ሀገራት ጉባኤ ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል መደረጉ ለሀገሪቱ ሌላኛው ስኬት ነበር ይላሉ፡፡

ባለፉት ሦስት ሳምንታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው ሁለት ታላላቅ ድሎች ሀገሪቱን፣ አህጉሪቷን እና ዓለምን የሚቀይሩ ናቸው ያሉት ሚስተር ፍሪማን “ግድቡ የኢትዮጵያ መጻዒ እጣ ፋንታ ተምሳሌት፤ የተፋሰሱ ሀገራት ጥምረት ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡

በአምስት ሀገራ የጋራ ጥምረት ላለፉት 15 ዓመታት የዘለቀው የብሪክስ አባል ሀገራት ጥምረት በቅርብ በደቡብ አፍሪካው ስብሰባው ስድስት ሀገራትን ቀላቅሎ ወደ 11 ከፍ ማለቱ የዓለም ምጣኔ ሃብታዊ ስሪት እስካሁን እንደነበረው እንደማይቀጥል ያመላከተ ክስተት ነበር ብለዋል፡፡

እንደ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሎውረንስ ፍሪማን እይታ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደገ የመጣው የብሪክስ አባል ሀገራት ጥምረት እንደ አንድ አማራጭ የእድገት አጋር እየታየ ነው፡፡ የራሱን የልማት ባንክ እስከ መመስረት የደረሰው ብሪክስ የመጻዒው ዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ተስፋ ነውም ተብሏል፡፡

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለአፍሪካ ሀገራት ሽያጭ ማቅረብ የሚችለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት ከሰሞኑ ተጠናቅቋል፡፡ አሁን ላይ ግድቡ 42 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይዟል ያሉት ሚስተር ፍሪማን በተያዘለት በግንባታው እቅድ መሰረት ከ7 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በታች ይቀረዋል ነው ያሉት፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 11 ተርባይኖች እያንዳንዳቸው ከ400 ሜጋ ዋት ኃይል በላይ የማመንጨት አቅም ይኖራቸዋል የሚሉት ሚስተር ፍሪማን 16 ሺህ ሜጋ ዋት በሰዓት የማመንጨት አቅም ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ሁለት ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጩ ነው ተብሏል፡፡

የግድቡ አሁናዊ ሂደት ኢንዱስትሪውን በማስፋፋት፣ የአምራች ዘርፉን በመደገፍ፣ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የኃይል አቅርቦት በማሟላት እና ለጎረቤት ሀገራት ኃይልን በሽያጭ ለማቅረብ የሚያስችል ነው የሚሉት ተንታኙ ሀገሪቱ ያቀደቻቸውን ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግሮች እውን በማድረግ በኩል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በተፋሰሱ የታኞቹ ሀገራት የውኃ ድርሻ ላይ ጉዳት አለማስከተሉ ደግሞ ሀገሪቱ በመርህ ደረጃ የያዘችውን በጋራ የማደግ ትልም የሚያሳካ ነው ይላሉ፡፡ ግድቡ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት መሰላል ከመኾኑም በላይ ለአህጉሪቷ ሀገራት በራስ አቅም የመልማት ተምሳሌት ኾኗል ነው ያሉት፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር እና የደሴ ከተማ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ ተጨማሪ የሞራል ድጋፍ ኾኖታል” ብርጋዴር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ
Next article“በ2016 ዓ.ም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለተመደቡበት የትኩረት መስክና ተልዕኮ የዝግጅት ሥራ ቅድሚያ ይሰጣሉ” የትምህርት ሚኒስቴር