“የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር እና የደሴ ከተማ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍ ለሠራዊቱ ተጨማሪ የሞራል ድጋፍ ኾኖታል” ብርጋዴር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ

241

ደሴ: መስከረም 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር እና የደሴ ከተማ አሥተዳደር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አዲስ ዓመትን በማስመልከት ከሕዝቡ የተሰበሰበውን ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የእርድ እንስሳት ድጋፍ አድርጓል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን እና የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርንና የሕዝብን ሰላም ለመጠበቅ መሥዋእትነት እየከፈለ መኾኑን ገልጸው ማኅበረሰቡም አጋርነቱን ለማሳየት ለሠራዊቱ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን አስረድተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ሕዝብ ለ2016 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓል ከ6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 59 ሰንጋ ፣103 ፍየሎች እና ሌሎች ቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሕዝብ ደግሞ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሰንጋ እና በጎችን ማበርከቱን የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ተናግረዋል።

የዞኑ እና የከተማ አሥተዳደሩ ሕዝብ ለ2016 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓል መዋያ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰንጋ እና ፍየሎችን ጨምሮ ሌሎች ቁሶችን ለሠራዊቱ አበርክቷል።

ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አሥተዳደር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ኅብረተሰቡ ለሠራዊቱ ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ አለመኾኑን ጠቅሰው ለተደረገው ስጦታ አመሥግነዋል።

የሕዝቡ ድጋፍ ለሠራዊቱ ተጨማሪ ስንቅና የሞራል ድጋፍ ኾኖታል ሲሉም ብርጋዴር ጀኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብሪታንያ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የ5 ነጥብ 9 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ አደረገች።
Next article“ግድቡ የኢትዮጵያ መጻዒ እጣ ፋንታ ተምሳሌት፤ የተፋሰሱ ሀገራት ጥምረት ማሳያ ነው” ሎውረንስ ፍሪማን