የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ የ104 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ።

51

ባሕር ዳር: መስከረም 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ልማት ባንክ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሃይል አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያግዝ የ104 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ፈንድ ማጽደቁን አስታወቀ። የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ያጸደቀው የገንዘብ ድጋፍ 52 ሚሊዮን ዶላሩ ከአፍሪካ ልማት ፈንድ የተገኘ ነው።
ቀሪው የገንዘብ ድጋፍ ደግሞ የባንኩ የብድር አጋር ከሆነው በኮሪያ-አፍሪካ የኢነርጂ ኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ስምምነት ከኮሪያ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ፈንድ የተገኘ ነው ተብሏል።

የባንኩ የኃይል ሥርዓት ልማት ዳይሬክተር ባቺ ባልዴህ ፕሮጀክቱ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ያለውን የኃይል ቋት አቅም በማሳደግ ታዳሽና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን የሚያሳድግ ነው ብለዋል። መንግሥት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን የኃይል አቅርቦት ጥረቶች የሚያግዝ ሲሆን አርብቶ አደሮች፣ አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮችና ሌሎች የማኅበረሳብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ 157 ኪሎ ሜትር እርዝማኔ ያለው የ400 ኪሎ ቮልት ባለ ሁለት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን እና ተያያዥ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በሐረር፣ በጅግጅጋ እና በፋፈም የሚደረጉ ግንባታዎችን ያካተተ ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅም በምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን የኃይል ማስተላለፊያ አቅም እንደሚያሰድግ ይጠበቃል።

ፕሮጀክቱ በቀጣይ ከሶማሊያ ጋር የኃይል ትስስር ለመፍጠር እንደ መነሻ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ምጣኔ ኃብታዊ ውህደትን በማሳለጥና ንግድን በማቀላጠፍ ረገድ አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው የተባለው። ፕሮጀክቱ መንግስት በክልሉ በ4 መቶ 62 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለምግብ ዋስትናና ለእንስሳት መኖ ልማት እየተገበረው ያለውን ግዙፍ የመስኖ ሥራ መርሃ ግብር በማገዝ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ተጠቁሟል ሲል የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዘረኝነት ሳይሆን ብሔርን ሽፋን ያደረገ የፖለቲካ ሽኩቻ ነው” አቶ አሽኔ አስቲን የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል
Next articleብሪታንያ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የ5 ነጥብ 9 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍ አደረገች።