
ባሕር ዳር: መስከረም 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዘረኝነት ሳይሆን ብሔርን ማዕከል ያደረገ የፖለቲካ ሽኩቻ ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማካሪ ኮሚቴ አባልና የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል አቶ አሽኔ አስቲን ተናገሩ። አቶ አሽኔ አስቲን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ብሔርና ሰፈርን ሽፋን ያደረገ የፖለቲካ ሽኩቻ መሆኑን ማወቅ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዘረኝነትን (Racism) እና ብሔርን (Ethnicity) አቀላቅሎ የማየት ችግር ይስተዋላል ያሉት አቶ አሽኔ፤ ሁለቱ ጉዳዮች ፈጽሞ የተለያዩ ቢሆኑም በዘረኝነት ምክንያት ጥቃት ደረሰብኝ የሚሉ ሃሳቦች እንደሚቀነቀኑ አመላክተዋል። ይሁንና በዘሬ ምክንያት ጥቃት ደረሰብኝ የሚሉ ሰዎች በብሔር ምክንያት አሊያም በሃይማኖትና በጎሳ የተነሳ በተቧደኑ ሰዎች ችግር የደረሰባቸው ናቸው:: ይህ የሚያሳየው ሀገራችን ውስጥ ዘረኝነት ሳይሆን ብሔርን ማዕከል ያደረገ ሽኩቻ መኖሩን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ዘረኝነት “አንተ ጥቁር ነህ፤ አንተ ነጭ ነህ” በሚል አሊያም እንደናዚዎች የእኛ ደም ከሌላው የተለየ በሚል እራስን የበላይ ለማድረግና ሌላውን ለማግለል የሚደረግ ጥፋት መሆኑን አቶ አሽኔ ገልጸዋል። ዘረኞች በአፓርታይድ ጊዜም ሆነ በተለያዩ ዓለማት በተነሱበት ወቅት እነሱ የሚጠቀሙበት የሃይማኖት ተቋም አሊያም የገበያ ስፍራቸው ውስጥ ሌላው እንዲገባ አይፈቅዱም ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
ብሔርተኝነት በአንጻሩ የፖለቲካ ፍላጎቴ አልተሟላም የሚል አካል ሃይማኖትን፣ ጎጠኝነትን፣ ቋንቋን ምክንያት በማድረግና ቡድን በመፍጠር አላማውን ለማሳካት የሚመርጠው አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል ኢትዮጵያ ውስጥም ብሔርን መነሻ አድርጎ የሚቀነቀኑ የፖለቲካ ፍላጎቶች አሉ፤ እነዚህ ፍላጎቶች አንድ ወገንን መደበቂያ በማድረግ የሚፈጸሙ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
አዳዲስ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ እንኳን ብሔርን መሠረት አድርገው ነው፤ ይህ የሚሆነው ፖለቲከኞች በቀላሉ የሕዝብን ቀልብ ለመግዛት የሚመቻቸው ማንነትን ወይም ብሔርን መሠረት አድርገው በሚሰራጩ መረጃዎች መሆኑን በማወቃቸው የተነሳ ነው ብለዋል። በመሆኑም ችግሩ ከታወቀ ለመፍትሄው ብሔርተኝነትን መሠረት ያደረገውን ችግር ለመቀነስ ምን መሠራት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ለመፍትሄውም ብሔርተኝነትን ማዕከል አድርገው የሚመጡ የፖለቲካ ሽኩቻዎችን ማስቀረትና በብሔር ላይ ተመርኩዘው የሚመጡ የአካታችነት ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን በስፋት መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል። የብሔር ማንነቶችና የቋንቋ ልዩነቶች ያሉና ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው ያሉት አቶ አሽኔ፤ ስለዚህ አካታችነትን በተለያዩ መስኮች ላይ ማስፋት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
በተለይ የወል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የብሔር ጥያቄ በማንሳት አሊያም የማንነትና የቋንቋ ሁኔታን በማንሳት ለሚመጡ ሰዎች የሚስተናገዱባቸውን የሕግ ማዕቀፎች ከወዲሁ በማዘጋጀት አካታችነትን ማጎልበት እንደሚገባ አስታውቀዋል። አንዳንዶች ዘረኝነት ነው አካታች እንዳንሆን ያደረገን፤ ችግራችን እሱ ነው ይላሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው በዘረኝነት ስም ወይም በሰፈር ስም የሚቀነቀን የፖለቲካ ሽኩቻ ነው ብለዋል::
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!