ዲጂታል የተማሪዎች መለያ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ ትምህርት ሚኒስቴር አሰታወቀ።

73

ባሕር ዳር: መስከረም 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ መርኃ ግብር በጋራ በመተባባር ዲጂታል የተማሪዎች መለያ ሥርዓት (የተማሪ መታወቂያ) ተግባራዊ አደረገ።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት የትምህርት ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን በትምህርት ተቋማት መደበኛ የተማሪዎች መለያ አድርጎ ለመተግበር ወስኗል።

ይህ ተነሳሽነት ኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፉን ዲጂታል ለማድረግና ለማዘመን በምታደርገው ጉዞ ወሳኝ ወቅት ላይ የተደረገ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ የተማሪዎች ዲጂታል መታወቂያ ጥቅም ላይ በመዋሉ ከሚገኙት ጥቅሞች መካከል ፈርቀዳጅ የሆነው የተማሪዎችን ማንነት በወጥነት መለየት የሚያስችል ስርዓት ማቋቋም ነው ብለዋል።

ይህም ዲጂታል መታወቂያ በሁሉም የትምህርት ተቋማት አበይት የማንነት ማረጋገጫ ሥርዓት ሆኖ እንዲያገለግል የሚያስችል እንዲሁም የአሰራር ድግግሞሽን በቀነስና በተማሪዎች የትምህርት ሰነዶች መካከል አንድነትና ቅንጅትን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

ከዚህም በላይ በላቀ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የግል መረጃን የማስቀመጥ እና የመጠቀም ደህንነትን በእጅጉ ይጨምራል፤ የውሂብ ጥበቃን ያረጋግጣል፤ ማንኛውም አይነት ጥሰቶችን በእጅጉ ይቀንሳል።
በተጨማሪም ቅንጅቱ ከፍተኛ የአሠራር ቅልጥፍና እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ መርኃ ግብር ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርዓያስላሴ በበኩላቸው የብሔራዊ መታወቂያ መርሃ ግብር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋራ ባደረገው ስምምነት እስከ አሁን 640 ሺህ ተማሪዎች ብሔራዊ መለያ ቁጥር ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ይህንንም በ2016 የትምህርት ዘመን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

መረጃው የትምህርት ሚኒስቴር ነው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስን ያረጋገጥንበት ነው” አቶ ደመቀ መኮንን
Next articleየጎንደር ከተማ ምክር ቤት በ4ኛ ዙር 11ኛ ዓመት 1ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ልዩ ልዩ ሹመቶችን አጸደቀ።