“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስን ያረጋገጥንበት ነው” አቶ ደመቀ መኮንን

49

ባሕር ዳር: መስከረም 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ የግድቡን አራተኛ የውኃ ሙሌት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በስፍራው ተገኝተው አብስረዋል።

በስፍራው ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በገንዘቡ፣ በሀሳቡ፣ በዕውቀቱና በልቡናው ተረባርቦ አሁን ካለበት ደረጃ መድረሱ ልዩ ታሪክ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ብርቱ ስንኾን እና ስንተባበር እንደዚህ አይነት ታሪክ እውነት ማድረግ ይቻላልም ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡ ብርቱ ኾነን ብዙ ችግሮችን እንሻገራለን፣ መተባበር፣ መደማመጥ፣ ወደ ዘላቂ መፍትሔ መጓዝና ሰላምን ማጽናት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

“ስናብር ነው ኢትዮጵያውያን የሚያምርብንም” ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡ በታሪካዊ ድላችን ላይ ቆመን ፣ የበለጠ ማበር፣ መተባበር እና የበለጠ ተሻጋሪ ኾኖ መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ባለፉት ዓመታት የሕዳሴ ግድብን ሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትን እየመሩ እንደቆዩ ያስታወሱት አቶ ደመቀ በሕዳሴው ግድብ ብዙ ጊዜ በመገኘት ዋና ዋና የታሪክ ምዕራፎችን የመከታታል እድል ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የግድቡን ማነቆ በመፍታት አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ማድረስ ስለመቻሉም አስታውቀዋል፡፡ አሁን ላይ ፈተናዎች እና ችግሮች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያውያን ተባብረው እና ተደማምጠው መፍታት እንደሚያሻም አንስተዋል፡፡ “የሕዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስን ያረጋገጥንበት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ለሀገራችን ከሠራነው ይልቅ ያልሠራነው ይበልጣል ያሉት አቶ ደመቀ ለዚያ የሚያበቃ ጉዟችንን ማጥበቅ አለብን ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙ ስም እና መለያ ያለው መልከ ብዙ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleዲጂታል የተማሪዎች መለያ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ ትምህርት ሚኒስቴር አሰታወቀ።