
መስከረም: 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ከሰሞኑ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ የሕዳሴ ግድቡ አራተኛ ሙሌት መጠናቀቅን ተከትሎ በስፍራው ሃሳባቸውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በርካታ ጥቅሞች እና ገጽታዎች እንዳሉት አንስተዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ አሁን ከያዘው ውኃ እየጨመረ ሲሄድ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለብዙ ዓመታት ሊያጠጣ የሚችል ሃብት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሕዳሴ ኃይል ነው፣ መብራት እናገኝበታለን፣ ኢንዱስትሪዎችንም እናስፋፋበታለን ነው ያሉት፡፡ ሕዳሴ ግደቡ መልካም አካባቢን እየፈጠረ ያለና ተፍጥሮን እያስዋበ መኾኑንም አንስዋል፡፡ ሕዳሴ ግድቡ ውብ የኾኑ ደሴቶች እንዳሉት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቅ የቱሪዝም መዳረሻ የመኾን አቅም እንዳለውም አንስተዋል፡፡
በሕዳሴ ግድቡ ለዓመታት በተግባር የተማሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በሕዳሴ ግድቡ የተማሩት የተግባር ትምህርት በየትኛውም ዩኒቨርሲቲ እንደማይገኝም አንስተዋል፡፡
በተግባር ለዓመታት የተማሩ ኢትዮጵያውያን ሳይበተኑ ማሠራት ከተቻለ ተጨማሪ ግድቦችን መገንባት የሚያስችልና ለሌሎች ሀገራት የሚተርፍ አቅም ማካበት ተችሏል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገራት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላላቅ ግድቦችና ኢንዱስትሪዎች እንደሚያስፈልጓትም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት ለሀገር አስፈላጊ የኾኑ ሥራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሌላ ሕዳሴ ግድብ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሕዳሴ ዳግም ዓድዋ ነው፣ የነጻነት፣ ራስን የመቻል እና ከልመና የመገላገልምልክት ስለመኾኑም ገልጸዋል። ለልማት ወደኃላ አልልም ፤ አልንበረከክም የማለት ምልክት ነውም ብለዋል፡፡ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ትምህርት እንደሚኾን ነው የገለጹት፡፡
የሕዳሴ ግድብ የውኃ ክምችቱ በራሱ ታላቅ አቅምና ሃብት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሱዳን እና ግብጽ ጥቅም ያለው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የተፋሰሱን ሀገራት የውኃ ድርሻ ሳናስቀር ለእኛም ሞልተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእኛም እድገት ለእነርሱም እድገት፣ ለእኛም በረከት ለእነርሱም በረከት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ቢኖሩባትም በቀላሉ የማትናጥ፣ የማትናወጥ፣ ያሰበውችውን የምታሳካ፣ በጫና የማትንበረከክ፣ ለነጻነቷ፣ ለክብሯ በቀላሉ የማትገዛ መሆኗን ዳግም ይህ ትውልድ ያረጋገጠበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የሕዳሴ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ ውኃ ሲይዝ ኢትዮጵያ ካሏት ሐይቆች የበለጠ ውኃ የመያዝ አቅም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ ሰው ሲተባበር እና አንድ ሲኾን ምን ሊሠራ እንደሚችል ማሳያ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ሀገራችን ተስፋና ብዙ ሃብት ያላት ድንቅ ሀገር መኾኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ያጣቸው ልቡና ያላቸው፣ የሰከኑ እና የሚያስተውሉ ልጆችን ነው ብለዋል፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ የስንዴ ልመናዋ ታሪክ ይኾናል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ለብዙዎች የምታጋራና አርዓያ የምትኾን ሀገር ትሆናለች ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ስትለማ፣ ግድብ ስትገድብና ሰላም ስትኾን የማይፈልጉ መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ፈተናዎቹ ኢትዮጵያን እንደሚያጠነክሯትም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ችግርና ፈተና ለመወንጨፍ፣ ለማደግ፣ ለመቀየር የምንጠቀምበት እንጂ የምንበረከክበት አይደለም ብለዋል፡፡ በየቀኑ ፈተና መኖሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተናው እያበረታ፣ እያጠነከረ፣ እያሰባሰበ፣ በተግባር እያስተማረ፣ ወደሚቀጥለው እድገት የሚወስድ መንገድ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መጪው ዘመን ተስፋ ሰጪ፣ በአፍሪካ ትክክለኛ ቦታዋን የምትይዝበት፣ በጥቂት ገንዘብና ስንዴ የማትንበረከክ፣ በነጻነት በትብብርና በፍቅር ከሌሎች ጋር የምትኖር፣ በዓለም ሕግ የምትገዛ፣ ወንድሞቿን የምታከብር፣ ሰጥታ የምትቀበል፣ በትብብር የምታምን፣ ከጎረቤቶቿ ጋር በፍቅር የምትኖር ሀገር መኾኗን በተግባር ታረጋግጣለች ነው ያሉት፡፡
” ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙ ስም እና መለያ ያለው መልከ ብዙ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡን በአንድ ገጹ ብቻ ማንበብ የማይቻል ስለመኾኑ አንስተዋል። የሕዳሴ ግድቡ መርካታ መገለጫ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ ሕዳሴ ምግብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግድቡ ያለውን የአሳ ልማት በሚገባ አልምተን ከተጠቀምን ሕዳሴ ምግብ ነው ብለዋል፡፡
ፈተናዎች ኢትዮጵያን እንደሚያበረቷት እና እንደሚያሻግሯትም ገልጸዋል፡፡ የሕዳሴ ግድብ እንዲሠራ መስዕዋት የከፈሉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በ2016 ዓ.ም ታላላቅ ለውጦች እና ድሎች የሚመዘገቡበት ዓመት እንደሚኾን ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል፡፡ ፈተናዎችም ይጨምራሉ ኢትዮጵያም ታሸንፋለች ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!