
ባሕር ዳር: መስከረም 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክን መሰረት ያደረጉ ብዥታዎች እንደሀገር ችግር እየፈጠሩ በመኾኑ ትውልዱ ቀጣይነት ባለው መልኩ ስለኢትዮጵያ እንዲወያይ ማድረግ ይገባል ሲሉ የታሪክ ተመራማሪው ባህሩ ዘውዴ (ኤመሬተስ ፕሮፌሰር) አስታወቁ።
ኤመሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደገለጹት ትውልዱን ስለኢትዮጵያ ጉዳይ ይበልጥ እንዲመካከር በማድረግ ታሪክን መሰረት ያደረጉ ብዥታዎች ይበልጥ ችግር እንዳይፈጥሩ መሥራት ይገባል።
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከቱ ጉዳዮች ቀደም ባሉ ዘመናት ያልታዩ ብዥታዎችና የአረዳድ ችግሮች አሁን ላይ ይበልጥ ተንሰራፍተዋል ያሉት የታሪክ ምሁሩ፣ ችግሮቹን በምክክር ግልጽ በማድረግ የሀገራችንን ዕድገት መሰረት እንዲይዝ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባሕሎችና ቋንቋዎች እንዳሉን የሚካድ ጉዳይ እንዳልኾነ የገለጹት ተመራማሪው፤ እሴቶቻችን ግን የመለያያ ምክንያቶቻችን ሳይኾን የመቀራረቢያ አውዶቻችን እንዲኾኑ መግባባትን መፍጠር ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።
በታሪክ ሂደቶች የተለያዩ ችግሮች አልነበሩም ማለት አይደለም፤ በደሎችም ኾነ በጎ ሥራዎችን ባለፉት የታሪክ አምዶች ላይ ተከናውነዋል ያሉት የታሪክ ምሁሩ፤ አሁን ላይ ግን አዲስ ጊዜ ነው። በመኾኑም ያለፉ ቁርሾዎችንና ጉንጭ አልፋ ክርክሮችን ተሻግረን መሄድ ይገባናል ሲሉ ሃሳብ ሰጥተዋል። የሚያዋህዱንና ለዕድገታችን የሚጠቅሙን ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ደግሞ አንዱ መንገድ ገንቢ ውይይት ማድረግ ነው ብለዋል።
ትውልዱን ዘላቂነት ባለው መልኩ ስለሀገሩ ጉዳይ ማወያየትና ስለኢትዮጵያ የተሰኙ መድረኮችን ማጠናከር የሕብረ-ብሔራዊነትን ሀሳብ ይበልጥ እንዲጎለብት ይረዳል ብለዋል። በሀገር ጉዳይ በተለያየ መንገድ የተፈጠሩ ብዥታዎችን ለማረቅ በዘላቂነት ትውልዱን ማወያየት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ጥርጣሬውንና አለመግባባቱን ለመቀነስ በግልጽ ጥናታዊ መሰረት የያዙ ጽሑፎችን በማቅረብ መመካከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
እውነተኛውን ታሪክና መሬት ላይ የተሠራውን ሥራ ሕዝብ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል ያሉት ፕሮፌሰር ባህሩ፤ ኢፕድ ጠቃሚ መድረኮችን እንዳዘጋጀ ሁሉ የታሪክ ምሁራንም በተደራጀና በሳይንሳዊ መንገድ መረጃዎችን ለሕዝብ ማድረስ አለባቸው ብለዋል።
በታሪኮቻችን ላይ የሰለለ መረጃ ሳይኾን ጥልቅና ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸውን መረጃዎች በመያዝ መጻፍና መናገር እንደሚገባ ጠቁመዋል። የኤመሬተስ ፕሮፌሰሩ በቀጣይም በታሪክ አረዳዳችን ላይ ይበልጥ ለመሥራት የሚረዳ የታሪክ ምሁራን ማኅበር በመቋቋሙ አዎንታዊ ውጤት ይኖረዋል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
እንደ ኢፕድ ዘገባ የተለያየ አጀንዳ ያለውን ማንኛውም ሰው ተነስቶ እንደልቡ የታሪክ መረጃ የሚለቅበትና ብዥታ የሚፈጥርበት አውድ መፍጠር ሳይኾን ትውልድን ሊገነባ የሚችልና ዕውነተኛነት ላይ የተመሰረተ የታሪክ አረዳድን መፍጠር ለሀገር ግንባታ መሰረት መኾኑን ኤመሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!