የኮርቻ ግድቡ የዋናውን ግድብ ውኃ የመያዝና ኃይል የማመንጨት አቅሙን እንደሚጨምረው ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ፡፡

95

መስከረም: 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተገነባው የኮርቻ ግድብ የግድቡን ውኃ የመያዝና ኃይል የማመንጨት አቅሙን እንደሚጨምረው ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በአዲስ ዓመት ዋዜማ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሕዳሴ ግድቡ ታላቅ ተስፋ ጥለውበታል፡፡ በ21 ኛው ክፍለ ዘመን በኩራዝ መብራትና በጭስ የሚሰቃዩ የኢትዮጵያ እናቶች እፎይ የሚሉበትን ዘመን ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ እየጠበቁ ነው፡፡

የሕዳሴ ግድቡን አራተኛ የውኃ ሙሌት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የአዲስ ዓመት ዋዜማ ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡

የሕዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት የ2016 አዲስ ዓመት መግባትን ተከትሎ ለኢትዮጵያውያን የተነገረ ታላቅ ብሥራት ሆኗል፡፡

በሥፍራው ለተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ የሰጡት የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በታላቁ የኢትዮያ ሕዳሴ ግድብ የኮሮቻ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ አገለግሎት መግባቱን ገልጸዋል፡፡

የኮርቻ ግድቡ ለሕዳሴ ግድቡ ታላቅ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የኮርቻ ግድቡ ባይኖር የግድቡ ከፍታ ሜትር በተፈለገው ልክ ሳይሆን ይቀር እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡ የኮርቻ ግድቡ ውኃ የመያዝና ኃይል የማመንጨት አቅሙን እንደሚጨምረውም ገልጸዋል፡፡

የኮርቻ ግድብ 5 ሺህ 200 ሜትር ርዝመት እና 50 ሜትር ከፍታ እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡ በኮርቻ ግድቡ አምስት ኪሎ ሜትር የመተላለፊያ መንገድ እንደተሠራለትም አብራርተዋል፡፡ የመተላለፊያ መንገዱ የዋሻ ውስጥ መንገድም እንዳለው የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ መንገዱ ግድቡን ለመቃኘት እንደሚያገለግልም አስታውቀዋል፡፡ ግድቡን የሚቆጣጠሩ መሣሪያዎች እንደተተከሉለትም ተናግረዋል፡፡

የዋናውን ግድብ በዘርፈ ብዙ መልኩ የሚጠቅመው ኮርቻ ግድቡ እንዳይሠራ አላስፈላጊ ጫናዎች እንደነበሩት ያነሱት ሥራ አስኪያጁ በተደረገ ጥናት ግድቡ በአስተማማኝ ሁኔታ መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

የኮርቻ ግድቡ በሚቀጥለው ዓመት አሁን ካለበት 20 ሜትር ከፍ ብሎ ውኃ እንደሚይዝም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በ2016 ዓ.ም በሕዳሴው ግድብ አምስት ተጨማሪ ዩኒቶችን ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ ነው” ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ
Next article“ታሪክን መሰረት ባደረጉ ብዥታዎች ላይ ትውልዱን ማወያየት ይገባል” የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ