“በ2016 ዓ.ም በሕዳሴው ግድብ አምስት ተጨማሪ ዩኒቶችን ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ ነው” ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ

56

መስከረም: 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ከሰሞኑ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ የሕዳሴ ግድቡን አራተኛ የውኃ ሙሌት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት አብስረዋል፡፡

በሥፍራው ለተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ የሰጡት የታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተገባደደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግድቡ፦ ግራ፣ ቀኝ እና መካከለኛ አካል እንዳለው የተናገሩት ኢንጂነር ክፍሌ ግራና ቀኙ የግድቡ ክፍል ከ635 እስከ 645 ደረጃ እንደሚሆን ነው የተናገሩት፡፡
የግራና ቀኙን ክፍል ለማጠናቀቅ ከዘጠኝ እስከ አሥር ሜትር ድረስ ብቻ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡

የግድቡን መካከለኛ ክፍል ለማጠናቀቅ ደግሞ 20 ሜትር እንደሚቀርም ገልጸዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ የግድቡ መካከለኛው ክፍል እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡ የሚቀረው ሥራ ግራና ቀኙን የግድቡን ክፍል የሚያገናኝ ድልድይ መሥራት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ከአራት ወር በኋላ የግድቡ ግራና ቀኝ ክፍል 645 ላይ መድረስ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

በግድቡ ኤልክትሮ መካኒካል ተከላዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ያስታወቁት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ግድቡ አሁን ላይ በሁለት ዩኒቶች እያመነጨ እንደሚገኝና በ2016 ዓ.ም ተጨማሪ አምስት ዩኒቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት የሕዳሴ ግድቡ በአጠቃላይ ሰባት ዩኒቶች እንደሚኖሩት ይጠበቃል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲሱ ዓመት ፍትሕን በመከተል ለሰብዓዊነት እና ለሰላም የምንቆምበት ሊኾን ይገባል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው
Next articleየኮርቻ ግድቡ የዋናውን ግድብ ውኃ የመያዝና ኃይል የማመንጨት አቅሙን እንደሚጨምረው ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ፡፡