አርባ ስምንት ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ የተለያዩ የበጎ አድራጎት እና የልማት ሥራዎች ማከናወኑን የባሕር ዳር በጎ አድራጎት ማኅበር አስታወቀ።

42

ባሕር ዳር: መስከረም 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበሩ የአዲስ ዓመት በዓልን አሥመልክቶ በአምስት ማዕከላት ከ5 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋርቷል።

የበጎ አድራጎት ማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አሕመድ ይማም እንደሚሉት ማኅበሩ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ገንብቶ አሥረክቧል፤ የጤና መድኅን ተጠቃሚ እንዲኾኑም አድርጓል፡፡ የመማሪያ ክፍል እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ትምህርት ቤቶችን እያስገነባ ይገኛል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ለሌሎች በጎ አድራጎት ማኅበራት ጭምር ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

የ2016 አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ለ5 ሺህ 350 አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና ወላጆቻቸውን ላጡ ወገኖች ከ722 ሺህ ብር በላይ በመመደብ በአምስት ማዕከላት የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አካሂዷል ተብሏል። ማሕበሩ ከተመሠረተ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ47 ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ ወጭ የተለያዩ የበጎ አድራጎት እና የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን ሥራ አሥኪያጁ ገልጸዋል።

ሥራ አስኪያጁ በቀጣይም አቅመ ደካሞችን ከመደገፍ ባለፈ በተለያዩ የልማት ሥራዎች በተለይም ደግሞ በማኅበራዊ ልማት ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ዝግባ የህጻናትና አረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ2 ሺህ 300 በላይ አጋዥ ለሌላቸው አረጋውያን እና ሕጻናት ድጋፍ አድርጓል። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ስለሽ ጌታቸው እንደገለጹት በ2000 ዓ.ም በ23 ሕጻናት እና 12 አረጋውያን ሥራውን የጀመረው ድርጅቱ በዚህ ወቅት 2 ሺህ 345 ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና የተቸገሩ ሴቶች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

የአዲስ ዓመት በዓልን አስመልክቶ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከቢአይካ፣ ከአማራ ባንክ የባሕር ዳር ሠራተኞች፣ ከሌሎች ድርጅቶች እና ግለሰቦች በተገኘ ከ800 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ለአረጋውያን የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር አካሂዷል። አጋዥ ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፍ የተደረገላቸው አረጋውያንም ስለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይ አጋዥ ለሌላቸው ተማሪዎች፤ አቅም ላጡ አረጋውያን በቋሚነት እራሳቸውን የሚደጉሙበት የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ሥርዓት ቢዘረጋ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትናንት ብዙ ነበረን፣ ዛሬ ግን ምንም የለንም፤ በበዓሉ እንድንደሰት ላደረጉልን እናመሠግናለን” ለበዓል ማዕድ የተጋሩ ወገኖች
Next articleየጎንደር ከተማ አሥተዳደር አመራሮች እና የመከላከያ ሠራዊት አባላትና መሪዎች የአዲስ ዓመት በዓልን በጋራ አክብረዋል፡፡