
ባሕር ዳር: መስከረም 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ከአረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ጋር ቾይዝ ውኃ ፋብሪካ በዓልን በጋራ አሳልፏል። ፋብሪካው የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በባሕር ዳር አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ለ1 ሺህ 500 አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋርቷል። ማዕድ ከተጋሩት ወገኖች መካከል ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በባሕር ዳር የሚገኙ ወገኖች ይገኙበታል።
ከድጃ ሙሐመድ ዛሬ ቾይዝ ውኃ ፍብሪካ ባዘጋጀው የበዓል መርሐ ግብር ላይ ማዕድ ሲጋሩ ያገኘናቸው እናት ናቸው። እንደ ዛሬው ቀን ገፍቶ እጅ ሳያጥራቸው በዓልን በደስታ፣ በክብር እና በፍቅር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያሳልፉ ነበር። ዛሬ ግን ቀን ገፋቸው፤ እጅም አጠራቸውና በበዓል ከምትሞቅ ቤታቸው ተፈናቅለው በወገኖቻቸው መዓድ ተጋሩ። እናት ከድጃ ለዓመታት የዘለቀው ኑሯቸው በወለጋ እንደነበር አጫውተውናል፡፡
በቀያቸው ወዳጅ አፍርተው፤ በቤታቸው ልጆች ወልደው ለወግ እና ማዕረግ አብቅተዋል። ክፉ ዘመን ያበቀለው የዘር ፖለቲካ መጥቶ ማንነታቸው ወንጀል እስኪኾን ድረስ ዓለምተኛ ነዋሪዎች ነበሩ። ዘር እየቆጠሩ ነዋሪን የሚያፈናቅሉ እና ሰበብ እየፈጠሩ ሰውን የሚያሳድዱ እኩያን ብቅ ብቅ ባሉ ጊዜ ግን እናት ከድጃ ከሞቀች ቤታቸው ወጥተው፣ 10 ቤተሰቦቻቸውን አስከትለው እና ሃብትና ንብረታቸውን ሳይወዱ ተገድደው፣ በትነው ለዘመናት የኖሩባትን ቀያቸውን በእንባ ተሰናበቷት። ቀን አልፎ ወደ ሞቀ ቤታቸው እስኪመለሱ ድረስ በሽምግልና ዘመናቸው በባሕር ዳር አዲስ ሕይዎት ጀምረዋል።
“ትናንት የሞቀ ቤት ነበረኝ፣ ከአንድም ሦስት ቤት፣ በወለጋ ስኖር ልጅ ድሬ ኩየ እኖርበት ነበር። ሸንኮራውና ሙዙ ተወው ሞልቶ ነበር፣ ያ ሁሉ ግን ዝግት እንዳለ ቀረ። ትናንት ብዙ ነበረኝ ዛሬ ግን ምንም የለኝም። የሞቀ ቤታችን ፈርሷል። ሃብታችን ተወርሷል። እኛ ግን ዛሬ በመከራ እንኖራለን” ነው ያሉኝ የትናንት ሕይወታቸውን ሲያስታውሱ።
አሁን ምንም እንደሌላቸው እና ልጆቻቸውን ለማስተማር እጅ እንዳጠራቸውም ነግረውኛል። ከቀያቸው ሲወጡ ምንም ነገር ሳይዙ ስለወጡ ሥራ ሠርተው ለመኖርም መቸገራቸውን ነው የሚገልፁት። “አላህ ይስጣቸው በአዲሱ ዓመት እንደ ሰው በዓልን ዋልን እንጂ ምንም አልነበረንም። በዓመት በዓሉ ቆሎ እንኳን መቁላት አልቻልኩም። በበዓል የለመድነው ነገር ብዙ ነበር። ነጋ መሸ ደጅ ማደር ሲሰለቸን ልጆቼን ይገድሉብኛል፤ ሃብቱ ሁሉ ይቅር ብዬ ትቼው ወጣሁ” ነው ያሉት እናት ከድጃ።
እናት ከድጃ መንግሥት ሲያደርግላቸው የነበረውን ድጋፍም ማቋረጡን ተከትሎ አሁን ላይ የእርሳቸው እና የቤተሰባቸው ሕይዎት አደጋ ላይ መውደቁንም ነግረውናል። “ወደፊት ምን እንደሚበጀን አናውቅም፡፡ ወደ ቀያችን ቢመልሱን ደስታውን አንችለውም፤ ያ ካልኾነ እንኳን ባለንበት መንግሥት ድጋፍ ቢያደርግልን ደስተኞች ነን” ብለዋል።
ከሞቀ ቤታችን ወጥተን አሁን ላይ የኪራይ ቤታችን ባዶ ነው እባካችሁ ድጋፍ አድርጉልን ብለዋል እናት ከድጃ በመልክታቸው። ተፈናቃዮቹ አሁን ላይ ለልጆቻቸው ያለችውን እየሰጡ እነርሱ ግን ጦማቸውን የሚያደርሩበት ቀን እንደሚበዛም ነግረውኛል። ቾይዝ ውኃ ስላስተወሳቸው እና በጋራ በዓልን አክብረው እንዲውሉ ስላደረገላቸው ሁሉ አመሥግነዋል።
በማዕድ መጋራቱ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ አሚናት እንድሪስም እንደ ከድጃ ሁሉ ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው የመጡ ናቸው። እሳቸውም በዓልን አስታውሰው በአንድ ላይ ስላዋሉን ደስተኞች ነን ብለዋል። ሌሎችም አቅመ ደካሞችን እንዲመልከቱ፣ የተቸገሩትን እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል።
ማዕድ ሲጋሩ ያገኘናቸው ሌላኛዋ እናት አዳነች ምህረት እሳቸውም እንደ ሌሎቹ ሁሉ ለበዓል መዋያ ምንም እንዳልነበራቸው እና ስለተደረገላቸው ሁሉ አመሥግነዋል። ምንም ነገር የለኝም፣ ችግርተኛ ነበርኩ፣ በዓልን በችግር አሳልፋለሁ፣ ዘንድሮ ግን በዓልን አብረው አዋሉን፣ የኑሮ ውድነቱ ከአቅማችን በላይ ኾነ፣ ምን እናድርግ? ነው ያሉኝ። የቤት ኪራይ እንኳን ልቀቁ እንባላለን፣ በወቅቱ የምንከፍለው እናጣለን፣ ኑሮው ከአቅማችን በላይ ኾኗል፣ በበዓል ከባዶ ቤት አውጥተው በጋራ ስላዋሉን እናመሠግናቸዋለን ነው ያሉት እናት አዳነች።
የቾይዝ ውኃ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተሾመ አሰፋ ፋብሪካቸው ጥራቱን የጠበቀ ውኃ ከማቅረብ ባለፈ የማኅበረሰብ አገልግሎት እንደሚወጣም ተናግረዋል። ፍብሪካው በዓመት ሦስት ጊዜ ማዕድ እንደሚያጋራም ነግረውናል። ፋብሪካው ለአካባቢው ማኅበረሰብ ውኃ በቦኖ ያደርሳል ያሉት ሥራ አስኪያጁ በችግር ምክንያት ቤታቸው ለፈረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
የ2016 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓልን በማስመልከት ለ1 ሺህ 500 አቅመ ደካሞች እና አረጋውያን ማዕድ ማጋራታቸውንም ገልፀዋል። ፋብሪካው በቀጣይም ለአቅመ ደካሞች እና አረጋውያን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። ቾይዝ ውኃ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች የሥራ እድል መፍጠሩንም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። ቾይዝ ውኃ ሀገር በፈለገው ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስ እና ድጋፍ የሚያደርግ ፋብሪካ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ አቅመ ደካሞችን እና አረጋውያንን መደገፍ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የአፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተዋበ አንለይ ፋብሪካው በርካታ ማኅበራዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀዋል። ሌሎች ተቋማትም ከቾይዝ ውኃ በመማር የማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!