“አዲሱን ዓመት በራሳችን እሴት ወደ ቀደመው ከፍታችን የምንነሳበት እንዲኾን ይቅርታ፣ ፍቅር እና ተስፋን ስንቅና ትጥቆቻችን እናድርግ” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

53

ባሕር ዳር: መስከረም 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አዲሱን ዓመት በራሳችን እሴት ወደ ቀደመው ከፍታችን የምንነሳበት እንዲኾን ይቅርታ፤ ፍቅር እና ተስፋን ስንቅና ትጥቆቻችን እናድርግ ብለዋል የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)። ዶክተር መንገሻ እንኳን 2016 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሳችሁ ብለዋል በመልእክታቸው።

የአማራ ሕዝብ በሀገር ሉአላዊነትና አንድነት መከበር ጉዳይ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም የማይናወጥ እምነት፤ የማይበረዝ ታሪክ፤ የማይታጠፍ ቃል ያለው ሕዝብ ነው ብለዋል ዶክተር መንገሻ፡፡ በሕዝቦች የእኩልነት ሚዛን እየሰፋ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን በቀስተ ደመና ሸምኗል፡፡ የአማራ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ተሰናስኖ በኢትዮጵያ ሀገራችን የረጅም ጉዞ ታሪክ ላይ የራሱን አሻራ አስቀምጧል ብለዋል፡፡

ዶክተር መንገሻ እንዳሉት ከሀገሩ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦናው ጋር ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ፤ ከእኛ ትውልድ የዘመን ደጃፍ ላይ ደርሷል፡፡ የውጭ ጠላት ሲገጥመን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ጠላቶቻችንን አሳፍረናል፡፡ ዛሬም የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን ግንባር ፈጥረው የከፈቱብንን ፈተና በመከላከያ ሠራዊታችን፣ በሌሎች የፀጥታ ኃይሎቻችን እና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቻችን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ዛሬም እንደትናንቱ በፅናት እንሻገረዋለን ነው ያሉት፡፡ በዶፍ ዝናብ እና በአስገምጋሚ የመብረቅ ነጎድጓድ ውስጥ ኾነን የባጀንባቸው የክረምት ወራትን አሳልፈን፤ በአበቦች ፍካትና በእጽዋት ፍሬ የተሞላችን ምድር የምንወርስበት የመፀው ወራት ጅማሬ ወደ ኾነው የአዲስ ዓመት ደርሰናል ብለዋል፡፡

ዶክተር መንገሻ በመልእክታቸው አዲሱ ዘመን የውይይት፤ የመከባበርና የመተባበር እሴቶቻችንን በውስጣችን አንግሰን፤ ለሕግና ሥርዓት የነበረንን ቀናዒነት በመካከላችን በማጽናት እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ወደ ቀደመው ከፍታችን የምንመለስበት ዘመን እንዲሆን ሁላችንም ልንተጋ ይገባናል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እንዳሉት “በብርቱ የምንመኛቸው የሀገር ሠላም እና የሕዝቦች አንድነት በአዲሱ ዓመት የበለጠ እንዲጠናከር ልቦናችንን በይቅርታ፤ በፍቅር እና በሠላም መንፈስ እንሙላ ፤ ከኋለኛው ዘመን የገጠሙንን ጉድለቶች ሁሉ መልሰን የመሙላት እድሉ የሚኖረንም ለነዚህ እሳቤዎች አዕምሯችን ለመክፈት እስከቻልን ድረስ ነውና” ሥለሆነም 2016 ዓ/ም የገጠሙንንና የሚገጥሙንን ችግሮች በውይይት፣ በመመካከርና በመቻቻል መንፈስ የምንፈታበት፣ ሕገወጥነትን አምርረን የምንታገልበት፣ ከቂምና ቁርሾ ወጥተን የሕዝባችንን ጥያቄዎች በመፍታት ተጠቃሚነቱን የምናረጋግጥበት የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የፍቅርና የብልፅግና ዓመት እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ ብለዋል!!!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የጋራ ስኬት ባለቤት ለመሆን ጠንክረን እንድንሠራ ጥሪዬን አቀርባለሁ” አቶ ተመስገን ጥሩነህ
Next article“ትናንት ብዙ ነበረን፣ ዛሬ ግን ምንም የለንም፤ በበዓሉ እንድንደሰት ላደረጉልን እናመሠግናለን” ለበዓል ማዕድ የተጋሩ ወገኖች