
ባሕር ዳር: መስከረም 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲሱን ዓመት በአዲስ ብሩህ ተስፋ ለመቀበል ከቂም በቀልና ቁርሾ ወጥተን ሀገራችን ብሎም ክልላችን ወደ ተረጋጋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዲሸጋገር ሁሉም የድርሻዉን ሊወጣ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው አሳሰቡ።
አቶ ደሳለኝ በሀገር ዉስጥ እና በውጭ የምትኖሩ ውድ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ! ብለዋል። ፈተናዎች ቢደራረቡም ከአባቶቻችን በወረስነዉ ፍጹም ጽናት እና አይበገሬነት ተስፋ ሳንቆርጥ በፈተና እና በተስፋ የተሞላ ጉዞን በድል ተሻግረን በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ለመሰነቅ እነሆ ለ2016 ዓመት ደርሰናል እንኳን ደስ አላችሁ ነው ያሉት።
እንደሕዝብ የገጠመን አሁናዊ የሰላም እጦት በየቦታዉ ሕገወጥ እንቅቅቃሴ እንዲበራከት፣ የሕዝባችን የእለት ከእለት እንቅስቃሴ እንዲገታ፤ ዜጎች ያፈሩት ሀብትና ንብረት እንዲወድም እና የሰዉ ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሁኗል። የዚህ እኩይ አላማ ተሳታፊዎችም ውድመትን እንደጀብድ ውድቀትን እንደጀግንነት በመቁጠር ያሳዩትን ችግር በመከላከያ ሠራዊታችንና በሕዝባችን ትግል ፍላጎታቸው ሳይሳካ ቀርቷል ብለዋል።
ይህን ያልተገራ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለመቀልበስ የመከላከያ ሠራዊታችን በሠራዉ አኩሪ ገድል በውስን ቦታዎች ውጭ በበርካታ አካባቢዎች ወደ መደበኛ ተግባራችን መግባት ጀመረናል። በዚህ ሰላም ማስከበር ሂደት መሥዋዕትነት ለከፈሉ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት እና ለሌሎች የጸጥታ አካላት እንዲሁም ለሰላም ወዳዱ ሕዝባችን ምሥጋናየ ላቅ ያለ ነዉ ብለዋል አቶ ደሳለኝ ጣሰው።
በክልላችን የታየውን ሕገወጥ እንቅስቃሴና የሰላም እጦት ወደ ተረጋጋና ዜጎች በሠላም ወጥተው የሚገቡበትን ሠላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር ሕይወቱን ሳይሳሳ መሥዋዕትነት እየከፈለ ካለው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ጋር አዲሱን ዓመት በጋራ ለማክበር በብዙ አካባቢዎች ከሀሳብና ገንዘብ ከማዋጣት አልፎ የተለያዩ የእርድ እንስሳትን በማቅረብ ያሳየው መነሳሳት የአማራ ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊታችን ያለውን ክቅርና ክብር ማሳያ ነው።
በዚህም የንቅናቄ ሥራ እንደ ክልል 278 በሬዎችን፣ 591 በግና ፍየሎችን፣ በጥሬ ገንዘብ 7,835,471፣ በቁሳቁስ 1,532,200 በአጠቃላይ 34,667,689 ብር የሚተመን ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ዛሬም እንደትናንቱ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን መኮኑን አስመስክሯል ብለዋል። አዲስ ዓመት በአዲስ ብሩህ ተስፋ ለመቀበል ከቂም በቀልና ቁርሾ ወጥተን ሀገራችን ብሎም ክልላችን ወደ ተረጋጋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዲሸጋገር ሁሉም የድርሻዉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!