“አዲስ ዓመትን ስናከብር በአብሮነትና በመረዳዳት ሊኾን ይገባል” የሃይማኖት አባቶች

42

ባሕር ዳር: መስከረም 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምዕመኑ አዲስ ዓመትን በአብሮነትና በመረዳዳት ስሜት ሊያከብር እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጸዋል። በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነገረ መለኮት መምህር አባ ጌዲዮን ብርሃነ የኢትዮጵያውያን መለያ የኾነውን አዲስ ዓመትን በአብሮነት ስሜት ማክበር ያስፈልጋል።

የክርስትናም ኾነ የእስልምና እምነት ተከታዮች በጋራ በመደጋገፍ በዓሉን ማሳለፍ ከቻሉ አብሮነታችንን ማጠናከር ይቻላል ያሉት መምህሩ፤ የበዓሉን የአንድነት ተምሳሌትነት ማጠናከር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ሕዝቡ አብሮነትን ለሚያጠናክሩ ትብብሮች የበለጠ ዋጋ ሊከፍል ይገባል ያሉት መምህሩ፤ ትናንት የነበረውን የአንድነት ስሜት በመረዳት ለአዲሱ ዓመት ሁሉም ዜጋ ለአብሮነት መረባረብ ይኖርበታል ብለዋል።

ሕዝቡ አዲሱን ዓመት ሲያከብር ማዕድ ማጋራቱ እንዳለ ኾኖ ጊዜው የትምህርት መጀመሪያ እንደመኾኑ የትምህርት ቁሳቁስ የሚቸገሩ ተማሪዎችን ባለን አቅም መደገፍ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የመማሪያ ቁሳቁስ አጥተው ከትምህርት ገበታ ውጪ የሚኾኑ ተማሪዎች መኖራቸውን የጠቆሙት መምህሩ፤ የተቸገሩትን ለመርዳት ኅብረት መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በዕድሮች፣ በመንፈሳዊ ማኅበራትና በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ማኅበራትን በመጠቀም በዘመቻ መልክ የመማሪያ ቁሳቁሶችን ማሰባሰብና ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይለዩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የተቸገሩ ዜጎችን ካልረዳንና ካልደገፍናቸው በልባቸው የሚበቅለው ፍቅር ሳይኾን የጭቆናና የመገፋት ስሜት ነው ያሉት አባ ጌዲዮን፤ አብሮነትን ሳናሳያቸው ካደጉ ለሀገር ወዳጅ ይኾናሉ ብሎ ማሰብ ያልዘሩትን እንደማጨድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አባ ጌዲዮን እንዳመለከቱት፤ አብሮነትን ለማጎልበት ሕዝቡ ቆም ብሎ አብሮነቱን እየሸረሸሩ ያሉ ነገሮች ምን እንደኾኑ በማሰብ የመረዳት ባሕሉን ሊያሳድግ ይገባል።

በመጨረሻም አባ ጌዲዮን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የጤና እንዲኾን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አማካሪ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው፤ አዲስ ዓመት የሰው ልጅ ህልሙን ለማሳካት አዲስ ምዕራፍና ዕድል የምናገኝበት በመኾኑ ፈጣሪን በማመስገን በአብሮነት ልናሳልፈው ይገባል ብለዋል።

በአዲስ ዓመት በአብሮነት ስሜት ከራስ አልፎ ለሀገርና ለማኅበረሰብ የተሻለ ነገር ለማምጣት ማሰብና መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ኡስታዝዝ አቡበክር እንዳመለከቱት፤ እንደሀገር የሚበጀው አብሮነት በመኾኑ መደጋገፍን በማጠናከር ለችግሮቻቸው የመፍትሔ አካል ለመኾን ወስኖ መንቀሳቀስ ይገባል ።

እንደ ሀገር የሚበጀን ተከባብረንና ተደጋግፈን ለጋራ ዕድገታችን ጥረት ማድረግ ነው ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ አዲሱን ዓመት ስናከብርም ሌላው ምን አድርጓል የሚለውን መመልከት ሳይኾን ወደራሳችን በመመልከት እኔ ለአብሮነታችን ምን አበርክቻለሁ የሚለውን ማሰብ ይገባናል ብለዋል።

እንደ ኢፕድ ዘገባ የሰው ልጅ ሲኖር ለእራሱ ስለኖረ ኖረ አይባልም ፤ እንደማህበረሰብ እርስበስርስ በመረዳዳት ችግራችንን በጋራ መፍታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሰጪነት ፈጣሪ የሰጠን ዕድል ስለኾነ በአዲሱ ዓመት የተፈናቀሉ ዜጎችን በመርዳት፣ የፈሰሱ እንባዎችን በማበስና የተሰበሩ ልቦችን በጋራ በመጠገን ልናሳልፍ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጨለማው አልፏል፣ ብርሃኑም ይመጣል”
Next articleየአፍሪካ ኅብረትና የኢጋድ መሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።