
ባሕር ዳር: መስከረም 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሁሉም በፊት ነበረ፣ ከሁሉም ጋር አለ፣ ሁሉንም አሳልፎ ይኖራል፡፡ በሁሉም ይገኛል፣ ሁሉንም ያውቃል፣ ሁሉንም ማድረግ ይቻለዋል፡፡ ዘመናትን የፈጠርካቸው፣ ዘመናትን የምትገዛቸው፣ ዘመናትን በጥበብህ የምታከታትላቸው፣ በፈቃድህ እንደፈጠርካቸው ሁሉ የምታሳልፋቸው አምላክ ትናንትን አሳልፈህ ዛሬን ሰጠህ፣ ዛሬንም አሳልፈህ ነገን ትሰጣለህ፡፡ ዘመናትን ትገዛቸዋለህ እንጂ ዘመናት አይገዙህም፣ ዘመናትን ትቆጥራለህ እንጂ ለአንተ ዘመን አይቆጠርልህም፣ ዘመናትን ታሳልፋቸዋለህ እንጂ አንተ ለዘላለም አታልፍም፤ ሕያው ነበርክ፣ ሕያው ነህ ሕያውም ሆነህ ትኖራለህ፣ መጀመሪያህ አይታወቅም መጨረሻም የለህም፡፡
ሰውን አብዝተህ ወደድከው፣ ተምሮ የሚያውቅበት፣ አውቆም የሚድንበት አዕምሮን ሰጠኸው፣ ጥበብን ይጠጣ ዘንድ ዕውቀትን አደልከው፡፡ ፍጥረታትን የፈጠርክ፣ ፍጥረታትንም አሳልፈህ የምትኖር ጌታ ዘመናትን እያሳለፍክ ዘመናትን ትሰጣቸዋለህ፣ ከጨለማው ዘመን እያወጣህ አዲስ ዘመን ታሳያቸዋለህ፣ ትናንት ያላደረጉትን የጽድቅ ሥራ ዛሬ ያደርጉ ዘንድ ሌላ እድል ትሰጣቸዋለህ፡፡
ምድር በዓደይ አበባ ተዋበች፣ ጀምበር ከተደበቀችበት የደመና ሽሽግ ወጣች፣ በደንገጡሮቿ ታጅባ ከቤተ መንግሥት እንደ ምትወጣ ልዕልት ተፍለቀለቀች፣ አብዝታም አበራች፣ ለምድርም ግርማና ሞገስን ሰጠች፡፡ የሚያስደነግጠው መብረቅ አልፏል፣ በተራራዎች ላይ የሚሳበው ጉም ተገፍፏል፣ በሰማይና በምድር መካከል የተዘረጋው ደመና ጠፍቷል፣ ሰማዩ ጠርቷል፡፡
ምድርን የሚያናውጿት ወንዞች ባዘቶ መስለዋል፣ ተራራዎቿን የሚያስደነግጡት ፏፏቴዎች እንደ ገነት ውኃ ጠርተዋል፤ ነጎዳውና ጉርምርታውም ከአሮጌው ዘመን ጋር ቀርቷል፤ ማዕበላት ረግተዋል፣ ማጓራትና መደንፋታቸውን፣ ጋራና ሸንተራራቹን ማስጨነቃቸውን ትተዋል፡፡
እነኾ አሮጌው ዓመት የሥልጣን ዘመኑን ፈጽሟል፣ ንግሥናውንም ለአዲሱ ዓመት አስረክቧል፣ ዳግም ላይመለስም ተሰናብቷል፡፡ አዲሱ ዘመንም አላፊ የኾነች ዘመኑን ተረክቧል፡፡ እድለኞች ሌላ ዘመን አይተዋል፣ እድል ያልቀናቸው ዘመንም የተፈጸመችባቸው ከአሮጌው ዘመን ጋር አልፈዋል፡፡ አዲሱን ዘመን በመናፈቅና በመጓጓት ተሰናብተዋል፡፡ ዓመታትን አሳልፈው ዓመታትን የተቀዳጁ የታደሉ ናቸው፣ ጨለማውን አልፈው ብርሃን ያዩም የታደሉ ናቸው።
ተጨማሪ ዘመን የተሰጣቸው፣ የትናንቱ ዘመን በቃችሁ ያልተባለባቸውም የታደሉና የተባረኩ ናቸው፡፡ ስለ ምን ቢሉ የተሳሳቱን የሚያርሙበት፣ ያስቀየሙትን ይቅርታ የሚጠይቁበት፣ ከተጣሉት ጋር የሚታረቁበት እድል ተሰጥቷቸዋልና፡፡
ልጆች ከቤታቸው ወጡ፡፡ ለአምላካቸውም ምሥጋናን ሰጡ፡፡ ከዓመት ዓመት ስላሸጋገራቸው፣ ተስፋና ምልክትም ስለሰጣቸው፣ ምድርንም ስላረጋላቸው ተመሥገን ይሉታል፡፡ አብዝተው ያመሠግኑታል፡፡
በጎጇቸው ወጥተው ወደ ተዋበች ምድር አቅንተው፣ አበባ ይቀጥፋሉ፤ የተወደደውን አበባም ይዘው ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ፡፡ በተመለሱም ጊዜ ከዘመን ዘመን የተሸጋገሩትን አሮጌውን ዓመት አሳልፈው የመጡትን ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ እያሉ ከያዙት አበባ ይሰጣሉ፡፡ መልካም ምኞትና ጽኑ ተስፋ ይመኛሉ፡፡
“ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም፣ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፣ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ፣ እንዲሁ ታሰናዳለህና፡፡ ትልምዋን ታረካለህ፣ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፣ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፣ ቡቃያዋንም ትባርካለህ፡፡ በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፡፡ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል፡፡ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፡፡ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፡፡ ማሰማሪያዎች መንጎችን ለበሱ፤ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፣ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም” እንደተባለ ጌታ ዓመታትን ያቀዳጃል፡፡ ኮረብታዎችም አምረዋል፤ ተውበዋል፤ ፍጠረታትም ይደሰታሉ፡፡ ምድርም በውበት ትጎናጸፋለች፤ አብዝታም ትዋባለች፡፡
በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባኤያት ደቀ መዝሙር መምህር ዲበኩሉ ሠንደቄ ኢትዮጵያ ሃይማኖትን ተከተለች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያለውንም አከበረች፣ ዘመኗንም ከእውነተኛው ቀዳች ይላሉ፡፡ ውኃዎች ከፍ ከፍ አሉ፣ መርከቢቱም በምድር ላይ ከፍ አለች፡፡ በውኃውም ላይ ትመላለስ ነበር፡፡ ውኃዎችም በምድር ላይ አምስት ወር ቆዩ፡፡ ጌታ ቀናቱን ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንትም መጻሕፍቱን አሜስጥረው የቀን መቁጠሪያውን የዘመን መለወጫውን ዘመን አረቀቁ፡፡ ይሄም በቅዱስ መንፈስ የተመራ፣ ረቂቅ የኾነ ምስጢር ያለበት፣ እውነተኛም የሆነ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ቀስተ ደመናው ይመለከቱታል፡፡ ቀስተ ደመናውም ለምልክት የተቀመጠላቸው፣ ለምስክርም የተሰጣቸው፣ ተስፋቸው ነው፡፡ እነርሱም ቀስተ ደመናውን ከሰማይ ይመለከቱታል፡፡ ቀስተ ደመናውን እይና የፈጠረውን አምሥግነው እንደተባለ ቀስተ ደመናውን እየተመለከቱ የፈጠረውን ያመሠግናሉ፡፡ ስለ ሰጣቸው ተስፋ፣ ስለ ሰጣቸው ምልክትም ለጌታቸው ምሥጋና ያቀርቡለታል፡፡ ቀስተ ደመናውም ለፍጥረት ሁሉ እንዳይጠፋ የተሰጠው የምልእክት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ቃል ኪዳኑን ያከበሩ ይከብሩበታል፡፡ ቃል ኪዳኑን የጠበቁ ይጠበቁበታል፡፡ የቃል ኪዳኑን አምላክ ያመኑና የተከተሉም በተስፋና በሰላም ይኖሩበታል፡፡
ኢትዮጵያ ለኖህ የተሰጠችውን ቃል ኪዳን ትቀበላለች፤ ቀስተ ደመናዋንም በሰማይ ላይ ትመለከታለች ይለሉ አበው፡፡ ኢትዮጵያ ሳታቋርጥ የምታገኛቸው በአንድ ዓመት አራት ክፍላተ ዘመናት አሏት፡፡ ሊቃውንት መጽሐፍ ቅዱስን ይዛው በመቁጠራቸው እና ምስጢርን በማሜስጠራቸው ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠሯ ከሌሎች ሀገራት ሁሉ ተለየች፡፡ የራሷንም የዘመን አቆጣጠር ይዛ ኖረች ብለውኛል፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ተለይታ አሥራ ሦስት ወራትን ትቆጥራለች፡፡ በአስራ ሦስት ወራትም የተገባውን ሁሉ ታደርጋለች፡፡
ክረምትን እንደ መከራ ዘመን ትቆጠራለች፣ መስከረምም እንደ ሰላምና ተስፋ ዘመን ትቆጠራለች፡፡ ክረምት አዳም በበደለ ዘመን እንደነበረው የመከራ ዘመን አምሳል ይቆጠራል፡፡ የክረምቱ ማለፍም አዳምና ልጆቹ ከሲኦል እንደ ወጡበት ወደ ቀደመ ርስታቸው እና ክብራቸው እንደተመለሱበት የፍስሃ ዘመን ይቆጠራል፡፡ የጳጉሜን ዘመንም የክርስቶስ ዳግም ምጻት የሚታሰብብበት፣ መብረቅ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ድንገት እንደሚመጣ ሁሉ የአምላክም መምጣት ድንገት እየተባለ የሚታሰብበት፣ የአምላክ ስምም የሚመሰገንበት ጊዜ ነው፡፡
መስከረም የደስታ እና የፍስሃ ዘመን ነውና ሊቃውንቱ ክርስቶስ በቀራንዮ ተስቀሎ ነብሳትን ከሲኦል ካወጣበት የደስታ ዘመን ጋር ያመሳስሉታል፡፡ ክረምቱ የምድራዊ ዓለም ምሳሌ ነው፡፡ ምድራዊ ዓለም መከራ ይበዛባታል፣ እሾህና አሜካላ ያይለበታል፣ መውደቅና መነሳት በሰው ልጆች ላይ ይበረክታል፡፡ ከመስረም በኋላ ያለው ጊዜ ደግሞ የመንግሥተ ሰማያት አምሳል ነው ይላሉ፡፡
ክረምት ላዩ ዝናብ፣ ታቹም ጭቃ ነው፤ የጭቃ እሾህም አለ፣ መብረቅና ንውጽውጽታም አለ፡፡ ገበሬ በጉምና በጭጋግ በተሸፈነች ምድር፣ እሾህና አሜካላ ባለበት መሬት ፍሬ አገኛለሁ ብሎ በተስፋ በክረመት የሰቀላትን ዘሩን አውርዶ ምድር ላይ ይበትናል፡፡ አዝእርቱንም ያርማል፣ ይንከባከባል፡፡ መስከረም በገባም ጊዜ ከአዝእርቱ አበባን ያያል፣ ፍሬንም ይመለከታል፡፡ አዲሱ ዘመንም የመንግሥተ ሰማያት አምሳል ነው፡፡ በአዲሱ ዘመን ተስፋ አለ፡፡ በአዲሱ ዘመን መልካም ነገርም አለና፡፡
አዲሱ ዓመት በሌላ በኩልም ከመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጋር ይያዛል ይላሉ መምህር ዲበኩሉ፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የብሉይ ኪዳን መጨረሻ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ነውና፡፡ መስከረም አንድ ቀን ወደ እስር ቤት ገባ፡፡ መስከረም ሁለት ቀንም በሰየፍ ተሰይፈ፡፡ ይሄም በዓል ከመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ጋር ይያዛል ነው ያሉኝ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓመታትን በወንጌላውያን ሰይማ ትቆጥራለች፡፡ አንዱን ዓመት ለማቴዎስ፣ አንዱንም ዓመት ለማርቆስ፣ አንዱንም ዓመት ለሉቃስ፣ አንዱንም ዓመት ለዮሐንስ ትሰጣለች፡፡ ይሄም ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ ትርጓሜና ምስጢር አለው እንጂ፡፡ ወንጌላውያንም መንፈሳዊነትን፣ ሰማያዊነትን፣ የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ወንጌላውያን ሕገ እግዚአብሔርን አስተምረዋልና፡፡ አራቱ ወንጌላውያን በአራቱ ኪሩቤልም ይመሰላሉ፡፡ አራቱ ኪሩቤል ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሥላሴን መንበር ተሸክመው ይኖራሉ፡፡ አራቱ ወንጌላውያንም ሃይማኖትን ከአምላክ ተምረው ዓለምን አስተማሩ፡፡ ዓለምም እነርሱ ባስተማሯት ትምህርት ጸናች ይላሉ አበው፡፡
እነሆ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር አሮጌው ዘመን አልፏል፡፡ አዲሱ ዘመንም ገብቷል፡፡ ተስፋንም ይዟል፡፡ ሰዎች ሁሉ ተስፋን ከዘመን ጋር የሚሰጣቸው አምላካቸውን አብዝተው እያመሠገኑት፣ ምድራቸውንም ሰላም ያደርጋት ዘንድ እየተማጸኑት ነው፡፡ እነሆ ጨለማው አልፏል፤ ብርሃኑም በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ይመጣል፡፡ ለዘመናትም ያበራል፡፡ ያም ብርሃን የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ነው፡፡
“ሌሊቱ አልፏል፤ ቀኑም ቀርቧል፡፡ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፡፡ በቀን እንደምንኾን በጽድቅ ሥራ እንመላለስ፣ በዘፈንና በስካር አይሁን፤ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፣ በክርክርና በቅናት አይሁን” እንዳለ መጽሐፍ ዓለም በድንግዝግዝ ተውጣለች፣ በመዳራትና በዝሙትም ተጠምዳለች፣ በክርክርና በቅናት አውታርም ተወጥራለች፡፡ ሌሊቱ ያልፍ ቀኑም ይቀርብ ዘንድ መልካሙን ነገር አድርጉ፡፡
ጥልና ክርክሩ ይራቅ፣ ቅናቱና ሽኩቻውም ይጥፋ፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የኖረው ሌሊት ይለፍ፣ ቀኑም ይቅረብ፣ የፍቅር፣ የሰላምና የአንድነት ጀምበርም ትውጣ፡፡ ጨለማውን ገፍፋ ትጣለው፡፡ የመከራውን ዘመንም ታሳልፈው፡፡ በአዲስ ዓመት የሚታየውን ተስፋውን ሁሉ እውን ታድርገው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!