
መስከረም: 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፋለስ የመጀመሪያው የግሪክ ፈላስፋ እና የሳይንሳዊ ሂሳብ ቀመርን ከፓይታጎረስ ጋር ሆኖ በጋራ የቀመረ የሥነ-ፈለክ ሰው (አስትሮኖመር) እንደነበር ይነገርለታል፡፡ አንድ ዓመት በ365 ቀናት እና አንድ ወር ደግሞ በ30 በቀናት እንዲከፋፈሉ ያደረገው የዓለማችን የመጀመሪያ የዘመን ቀማሪ ጠበብት እንደ ነበርም የሳይንሱ ዓለም ታሪክ ይነግረናል፡፡
ሳይንሳዊ ለሆነው የሥነ-ፈለክ እሳቤ እና ምርምር መሰረቱ ከሃይማኖት ተቋማት የተገኘው ጥንታዊ እውቀት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በርካታ ጥንታዊ የዓለም ሀገራት የዘመን ስሌትን ቀመር ለማምጣት ፀሐይን፣ ጨረቃን እና ከዋክብትን እንደ መነሻ አድርገው ተጠቅመዋል፡፡ ሀገራት ዓመትን ለመቁጠር ዘመንን ለመቀመር ከፍጥረት ተቀዳሚው አዳም እስከ ክርስቶስ መወለድ ደረስ በተለያየ መንገድ ከፋፍለው ያዩታል፡፡
ክርስቶስ ኢየሱስ የፍጥረት ተቀዳሚ የሆነውን አዳም ከፈጠረው በኋላ በገነት ለሰባት ዓመታት አሳልፏል ይላሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለዘመን አቆጣጠር ሲናገሩ፡፡ ከአዳም መፈጠር አንስቶ ዓመተ ፍዳን እና ዓመተ ምህረትን አጠቃለው በአንድ ሲቆጥሩ ደግሞ ዓመተ ዓለም ይሉታል፤ ይኽም 7 ሺህ 516 ዓመቱ መስከረም 1/2016 ዓ.ም ይጀምራል ይሉናል፡፡
አዳም በገነት እያለ ትዕዛዝን ተላልፎ በሰባተኛው ቀን ከገነት ሲባረር ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ በአምሳሉ ተወልዶ ከሰማያት ወርዶ እንደሚያድነው ቃል ገብቶለት ነበር የሚሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መምህር የሆኑት ማዕበል ፈጠነ ናቸው፡፡ ይኽ 5 ሺህ 500 ዘመን “ዘመነ ፍዳ” ተብሎ ይጠራል ይላሉ፡፡ የፍጥረት ተቀዳሚው አደምም የመዳኑ ቀን እንደሚመጣ ለልጆቹ ነግሯቸው ነበርና በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት ተለያይተው ይቆጥሩ እና ይጠብቁ ነበር ይላሉ፡፡
የአዳም የመዳን ተሰፍው ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱን ተከትሎም ዘመነ ፍዳ ተጠናቆ የአዳም መዳን ተበሰረ፤ ይኽም “ዓመተ ምህረት” ሲባል 2 ሺህ 16 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ከአዳም መፈጠር ጀምረን ዓመተ ፍዳ እና ዓመተ ምህረት በአንድ ላይ ሲጠሩም “ዓመተ ዓለም ይባላል” ይላሉ መምህር ማዕበል፡፡
የኢትዮጵያ የዘመን ስሌት ቀመር ባሕረ ሃሳብ ሲባል ትርጓሜውም “ባሕር ስንል ዘመን፤ ሃሳብ ስንል ሥሌት ማለታችን ነው” የሚሉት መምህር ማዕበል ቀመሩም በሦስት ተከፍሎ ይታያል ይላሉ፡፡ የመጀመሪያው ዓመተ ፍዳ ወይም ዓመተ ኩነኔ ሲባል 5 ሺህ 500 ዘመናትን ይሸፍናል፡፡ ይኽንን ጊዜም የቀመር ሊቃውንት በቀመር ከፍለው የኩነኔ ዓመት በማለት ይጠሩታል ይሉናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ዓመተ ምህረት ነው ከሰማይ ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ከዓመተ ኩነኔ ወደ ዓመተ ምህረት መሸጋገሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
ከአዳም የገነት ስንብት እስከ ክርስቶስ መምጣት ባለው ዓመተ ፍዳን 5 ሺህ 500 ዘመናትን ያሰላችው ኢትዮጵያ ከክርስቶስ መወለድ ጀምራ ደግሞ 2 ሺህ 16 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር ስሌት መሰረትም ዓለም ከተፈጠረ 7 ሺህ 516 ዓመታት ሆነውታል ይላሉ መምህር ማዕበል፡፡
ባሕረ ሃሳብ እንደሚነግረን በፀሐይ አቆጣጠር ዓለም ከተፈጠረች 7 ሺህ 516 ዓመታት ተቆጥረዋል የሚሉት መምህር ማዕበል በጨረቃ አቆጣጠር ደግሞ 7 ሺህ 746 ዓመት ከ8 ወር ከ20 እለት ሆኖታል ይሉናል፡፡
ዘመን በሰዎች ሲቆጠር የሰው ልጅ ደግሞ በዘመን ይሰለጥናል፤ ምክንያቱም የዘመን ጌታው ሰው ነውና ብለውናል፡፡ አሮጌው አልፎ በአዲሱ ሲተካ መጪው አዲስ ሲባል ያለፈው ደግሞ አሮጌ ተብሎ ወደ ታሪክ ኮሮጆው ይወርዳል፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!