
ከሚሴ: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በአካባቢው ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰንጋዎችንና ፍየሎችን ለአዲስ ዓመት የበዓል ስጦታ አበርክቷል።
በርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ እንዳሉት የመከላከያ ሠራዊቱና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሕዝብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ የሀገራችን ብቸኛው የኾነ አይተኬ ኃይላችን ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ በ302ኛ ኮር የ73ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ሌተናል ኮለኔል ጀማል አማን ሠራዊቱ ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል የሚሰጠውን ግዳጅ በድል እየተወጣ መኾኑን ገልጸው ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
የአካባቢው ማኀበረሰብ ለሠራዊቱ ደጀን በመኾን የበኩሉን እየተወጣ ነውም ብለዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪና የሰላምና ሕዝብ ደኀንነት መምሪያ ኀላፊ አሊ መሀመድ በሽር ኀብረተሰቡን በማሳተፍ ከ22 በላይ ሰንጋዎችንና 25 ፍየሎችን ለጸጥታ መዋቅሩ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ይማም ኢብራሒም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!