
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአብሮነት ቀንን በማስመልከት መልእክት አስተላልፏል።
ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦
አብሮነታችን ለሰላም !!
አብሮነት ለሰው ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብር ወሳኝ ሚና ያለው እሳቤ ነው። አብሮነት የተለየ ማንነትን፣ ባህልን ወይም ሃሳብን የሚያከብርና የሚያስተናግድ በሰላም አብሮ ለመኖር መሰረት የሆነ ነው።
የአብሮነት ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር የተደረገው የሀገራችን ሕዝቦች በቦታ አቀማመጥ፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በቋንቋ ልዩነቶች ምክንያት የሰው ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ነው።
በሌላ አገላለጽ በልዩነቶች ምክንያት በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብና አብሮነት ለሰው ልጆች ተሳስበው ለመኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው።
የሰው ልጆች አንዱ የሌላውን ሰብዓዊ መብት በማክበርና ከሌሎች ጋር በመቻቻል መኖር ለሕዝቦች ወሳኝ መሆኑን ግንዛቤ ለማስረፅ ጭምር ነው።
ሰዎች በተፈጥሮ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በማንነት ወዘተ የተለያዩ በመሆናቸው የሰው ልጆች አብሮ የመኖር ኅልውና የሚረጋገጠው በአብሮነት ብቻ ነው።
ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል የመተባበርና አብሮ የመፋለም እሴት ዛሬም ጎልቶ ይታያል። ለዚህም በትናንናው ዕለት የመጨረሻው እና የአራተኛ ዙር የውሃ ሙሌቱ በስኬት የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሌሎች ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉም ዜጋ በጋራ መሳተፋቸው ጉልህ ማሳያ ነው።
ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሕዝቦችን የሰላምና የአብሮነት ፍላጎት የማይመጥኑ፣ ትብብርና ወንድማማችነታቸውን ከማጠናከር ይልቅ የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያሻክሩ፤ በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት ከማጉላት ይልቅ ልዩነት ላይ የሚያተኩሩ ክስተቶች አጋጥመዋል ቆይተዋል።
በተከሰቱ ግጭቶቹ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ደርሷል እንዲሁም ዜጎች ለዓመታት ከኖሩባቸው ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ይህን መሰል የአብሮነት እሴቶችን የሚሸረሽሩ አካሄዶች መታረም ካልቻሉ የሕዝቦች ዘመናት የተሻገረው አብሮነትን ከመሸርሸር አልፎ ሀገሪቱ ለማንም መሳቂያ መሳለቂያ ሊያደርጋት እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው።
የአማራ ሕዝብ ጠንካራ ክልል የሚሆነው ሕዝቦቹ በአብሮነት መቆም ሲችሉ ነው። እንደ ክልል ወደኋላ መለስ ሲባል በተመጣበት መንገድ ክፍተቶች አልነበሩም ባይባልም፣ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም ለነገው ትውልድ የሚሻገር ሰላም፣ አብሮነትና አንድነትን ማረጋገጥ ከዛሬው ትውልድ የሚጠበቅ ነው።
በእርግጥ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን የሚሉ አካላት በሚያሰራጩት ትርክትና የተዛባ አስተሳሰብ እንጂ፣ የክልላችንን ሕዝብ ለዘመናት የገነቡት ትስስር፣ መስተጋብርና የአብሮነት እሴቶች ለመለያየት የማያስችሉና የተሳሰሩ መሆናቸውን ማንም የሚገነዘበው እውነታ ነው።
አብሮነት ከሌለ ወይም ከተሸረሸረ ለእርስ በርስ ግጭት እና የክልሉን ሕዝብ ደህንነት ስጋት የሚሆኑ አደጋዎችን ያስከትላል። ስለሆነም ጠንካራ ክልል እንዲኖረን የአብሮነት እሴቶቻችንን ልንከባከበው ይገባል።
መልካም የአብሮነት ቀን !!
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!