የደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ለአዲስ ዓመት በዓል መዋያ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የእርድ እንስሳት ድጋፍ አደረጉ።

227

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ለዘመን መለወጫ በዓል መዋያ የሚሆን ከ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የእርድ እንስሳት ድጋፍ አደርገዋል።

የዞኑ ሕዝብ በአካባቢው ለተሰማራው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ያወሱት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ሕዝቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ አጋርነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ሠራዊቱ መስዋዕትነት እየከፈለ ሀገርና ሕዝብ እየጠበቀ መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው ኀብረተሰቡም ሁለተናዊ ድጋፍ በማድረግ ግዳጁን በስኬት እንዲወጣ ደጀንነቱን አጠናክሯል ብለዋል፡፡

የዞኑ ሕዝብ ለ2016 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓል መዋያ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት 59 ሰንጋ በሬዎችና 103 ፍየሎች ጨምሮ ሌሎች ቁሶችን ማመቻቸቱን አስታውቀዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ በበኩላቸው የደቡብ ወሎ ዞን ህዝብ እያደረገ ያለው ሁለተናዊ ድጋፍ ለሰራዊቱ ብርታትና ስንቅ እንደሆነው ጠቁመዋል።

ሕዝቡ ቀደም ሲልም ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያስከበረ ጀግና በመሆኑ ያኮራናል ብለዋል፡፡

ዛሬም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለዘመን መለወጫ በዓል መዋያ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በቀጣይም ኅብረተሰቡ ከጎናቸው ተሰልፎ የተለመደ ትብብሩን በማጠናከር የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ የድርሻውን መወጣቱን እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፈ።
Next article“ጠንካራ ክልል እንዲኖረን የአብሮነት እሴቶቻችንን ልንከባከበው ይገባል” የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት