
ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመን ተለወጠ ሲባል የጸሃይ ዑደትን፣ የመሬት ዙረትን፣ የጨረቃ ደምቀትን እና የወንዝ ሙላትን ለውጦች የሚያመለክት ብቻ አይደለም፡፡ ዘመን ሲለወጥ አብረው የሚለወጡ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ባሕላዊ ገጾች አሉ፡፡ አንድ ዓመት የ13 ወራት ልዩ ጸጋ፤ የ365 ቀናት ኑባሬ እና ውጣ ውረድ ፍጻሜ ተደርጎ ይወሰዳል። ክረምት የወለደው ጭፍናው ወራት አልቆ የብርሃናማው ወራት መምጣት ተብሲርም ነው።
አሮጌው ዘመን አልቆ አዲሱን ዘመን ሲተካ በአዲስ እሳቤ እና ተስፋ ስለመቀበል አዲስ ዓመት በአዲስ ይከበራል፡፡ አዲስ መንፈስ፣ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ራዕይ እና አዲስ ለውጥም ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ዘመንን ስትቀይር የዘመን ስሌትን ብቻ ሳይሆን የዘመን ሰንኮፍንም ለመንቀል ተስፋ ታደርጋለች።
ተስፈኘዋ ኢትዮጵያ በተስፋዋ ምድር ያለፈው ዘመን መከራ እና ጨለማ በአሮጌው ዘመን ተወራርዶ በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ሰንቃ ሁሌም በአዲስ እንደ አዲስ ትቀበላለች። አመስጋኟ ኢትዮጵያ የከረመው ዘመን መከራ እና ስቃይ ባለፈው ዘመን ይብቃ ብላ አዲሱን ዘመን በብሩህ ተስፋ እና በአዲስ መንፈስ ትቀበላለች።
ዘመን አልቆ ዘመን ሲተካ ካለፈው ተምሮ የሚመጣውን አሳምሮ መቀበል እንጂ እንዳለ ማስቀጠል አልተለመደም። ዘመንን በዘመን መተካት ብቻ ሳይሆን ከዘመን የተስማማ እና ዘመኑን የሚመጥን እሳቤም በአዲሱ ዓመት ይጠበቃል። ተፈጥሯዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ምድር እንደ ጅረት የማያቋርጥ ሂደት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም ሀገራት የተለየ የዘመን መለወጫ ጊዜ እና ወቅት አላት። በኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም የተለየ የቀን መቁጠሪያ እና የወራት እርዝማኔ ይስተዋላል። የራሷ የሆነ ወጥ እና ጥንታዊ ማንነት፤ ፊደል እና ጽሕፈት፣ እሴት እና ውበት የሚስተዋልባት ኢትዮጵያ የዘመን ስሌቷም ረቂቅ እና ምክንያታዊ ነው። በምክንያት እና በእምነት የጸናችው ኢትዮጵያ ያለምክንያት የሚከበር፤ ያለእምነት የሚተገበር እሳቤ የላትም።
ጥንታዊ ስልጣኔ የተጀመረባት፣ አኩሪ ገድል የተፈጸመባት እና የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የዘመን መለወጫዋ ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ እና ከአዲስ እሳቤ ጋር የተገናኘ ነው። በጋውን በክረምት፣ ሃሩሩን በጅረት፣ ድርቁን በውኃ ሙላት ሸኝታ በአበቦች በፈካ፣ ጅረት በተለካ እና ጨለማው በነጋ ጊዜ አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ትቀበላለች።
ከክረምቱ ብርድ ለመሸሸግ በየጥሻው የከረሙት አዕዋፍት ከየጥሻው ብቅ ብቅ እያሉ በሚያሰሙት ሕብረ ዝማሬ አዲስ ዘመን ስለመቃረቡ ተፈጥሯዊ ምስክሮች ይሆናሉ። የውኃ ሙላት ጎድሎ በጀረት ሲተካ አስፈሪው ክረምት አልቆ መስከረም ስለመጥባቱ እና አዲስ ዘመን ስለምጣቱ ምልክት ይሆናል። የአረንጓዴው ልምላሜ የዕጽዋቱ ተፈጥሯዊ ዝማሜ አዲስ ዘመን መምጣቱን ያበስራል።
ያለፈው ዘመን ፍጻሜ እና የመጭው ዘመን ጅማሬ የዘመን ድልድይ በሆነችው ወርሃ ጳጉሜን ይበሰራል። የዘመን ድልድይ በሆነችው ጳጉሜን ህጻናት በጥምቀት እናቶች በእጥበት ያለፈውን ዘመን እድፍ እና ጉድፍ ያለቃልቃሉ። ጳጉሜን በቀሪው ዓለም የማትታወቅ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የምትናፈቅ አጭር ግን ሙሉ የሽግግር ወር ናት።
በአዲስ ዘመን ጅማሬ ጠዋት ህጻናት አደይ አበባ አሰባስበው ለቤተ ዘመድ የአዲስ ዓመት ጅማሬ ብስራት አድርገው ያበረክታሉ። እንቁጣጣሽ ሲሉም በአዲስ ዘመን ጣጣችሁ በእንቁ ይቀየር ሲሉ መልካም መኞታቸውን ይገልጻሉ። የነገ ሀገር ተረካቢዎች እና የንጹህ ልብ ባለቤቶች የሆኑት ህጻናት የአዲስ ዘመን ብስራት ዓዋጅ ነጋሪዎች ይሆናሉ። የአባቶች በረከት እና የእናቶች ዳረጎት ለህጻናቱ ብስራት የሚሰጥ ምላሽ ይሆናል። ዘመን በትውልድ ቅብብሎሽ ድካ እየተለካ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር እንዲህ ይነጉዳል።
አዲስ ለብሰው እና ጻዕዳ ተጎናጽፈው አዲስ ዓመትን የሚቀበሉት ኢትዮጵያዊያን መጭውን ዘመን ይመስላሉ። መልካም ያሉት ሁሉ ቀጥሎ መጥፎ የሚሉት ሁሉ ተጥሎ አዲሱ ዓመት በአዲስ ተስፋ እንደ አዲስ ይጀመራል። እህል እና መሬትን ሰኔና ግንቦትን አስማምቶ ያንን ጭፍና ዘመን ያሻገረን ፈጣሪ ከተወራው እና ከተፈራው ይሰውረን ሲሉም በፌጦ ፍትፍት እና በበቆሎ እሸት የአዲስ ዓመት ማለዳን ይቀበሉታል። ቡናው ተፈልቶ ፈንድሻው ፈክቶ፤ ጠላው ተዘንብሎ ጮማው ተዘልዝሎ፤ ጎረቤት ተጠርቶ የሩቅ ዘመድ መጥቶ ዘመን በዘመን አዲስ እየተባለ ይለወጣል።
ሁልጊዜም አዲስ ዓመትን በተስፋ በምትቀበለው ኢትዮጵያ ዘንድ ተስፋ አስቆራጭ ፈተናዎች ነጥፈውላት አያውቁም። ፈተና ከጠላቶቿ፤ ጽናት ደግሞ ከልጆቿ የማይነጥፍባት ኢትዮጵያ ወደቀች ሲሏት ተነስታ፤ ደከመች ሲሏት በርትታ የልጆቿ ኩራት የጠላቶቿ ስጋት ትሆናለች።
ኢትዮጵያዊያን የሚናፍቁት የኢትዮጵያዊ ዘመን አንጥረኞች ደግሞ እያለፉ በሚያጸኗት፣ እየወደቁ በሚያነሷት እና እየተረሱ በሚያስታውሷት ልጆቿ ብርቱ ክንድ ላይ የተመሰረተ ነውና ምስጋና ለእነርሱ ይሁን።
በተስፋው ምድር አዲስ የተስፋ ዘመን ነጋሪት በአዲስ ዓመት ይጎሰማል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!