
ባሕር ዳር ጥር 9/2012ዓ.ም (አብመድ) በጎንደር ከተማ የፋሲለደስ ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ያለበትን የማስተማሪያ ክፍል ጥበት ለመቅረፍ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ተጨማሪ ክፍል ሊያሰሩ ነው።
በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቀድሞ ተማሪ ተወካዮች የክፍል ጥበቱን ለማቃለል ያለመ የመሰረት ድንጋይ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ዛሬ አስቀምጠዋል። የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ግንባታው ባለ አራት ፎቅ ሆኖ የሚገነባና 24 ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች የሚኖሩት ነው፡፡
ከቀድሞ ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆኑትና ፕሮጀክቱን ለማሰራት በማስተባበር ላይ የሚገኙት አቶ አባይ ዘለቀ የግንባታው ጠቅላላ ወጭ እስከ 20 ሚሊዮን ብር ሊደርስ እንደሚችል ለአብመድ ተናግረዋል። በሶስት ዓመታት ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንደታሰበም አስረድተዋል። ሌሎች የቀድሞ ተማሪዎችንም በማስተባበር ትምህርት ቤቱን ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ እየተሰራ እንደሚገኝ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም ተናግረዋል፡፡
ለግንባታው 5 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ደርባን ሲሚንቶ ፋብሪካ መስጠቱን የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሌሎች አካላት የሚያደርጉት ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።
የፋሲለደስ ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ከ1934ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ትምህርት ቤቱ ከምስረታው አሁን እስካለበት ጊዜ ድረስ በርካታ ምሁራንን ያፈራ እንደሆነም ይነገራል። ይሁን እንጅ ግንባታዎቹ አሁንም በመፈራረስ ላይ ናቸው።
ለዓመታት በአንድ ክፍል ከ80 እስከ 90 ተማሪዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡ ይህም በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ:- ሀይሉ ማሞ