“ፋብሪካው ከተመሰረተ ጀምሮ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጥቷል” የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ

26

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ አዲሱን ዓመት አስመልክቶ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል፡፡

የፋብሪካው ዋና ሥራ አሥኪያጅ ወርቁ ባየ እንዳሉት ፋብሪካው ከተቋቋመ ጀምሮ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ አረጋዊያን፣ የጤና መድኅን መሸፈን ላልቻሉ ዜጎች እና አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

አሁን ላይም ፋብሪካው አዲሱን ዓመት መሠረት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የፊኖ ዱቄት፣ የዘይት እና የዶሮ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በቀጣይም ፋብሪካው ከሚያገኘው ትርፍ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እንደሚወጣም ገልጸዋል፡፡

አብሮነት የኢትዮጵያዊያን የቆየ መልካም እሴት መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በዓሉን ስናሳልፍ በመተሳሰብ፣ በመረዳዳት እና በመተጋገዝ በጋራ ማሳለፍ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

አረጋዊያንም ለተደረገላቸው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በዓሉን ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋራ እንደሚያሳልፉም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ በሚያመርተው ምርት ከዚህ በፊት ሀገሪቱ ያላትን የውኃ ሀብት ለመጠቀም ከውጭ ታስገባ የነበረውን ግብዓት ማስቀረት ችሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ በኢትዮጵያ ለሚገነቡ የውኃ ግድቦች፣ የንጹህ መጠጥ የውኃ ተቋማት ግብዓቶችን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የአበባ ልማት ሼዶችን በማምረት ከአማራ ክልል ባለፈ በመላ ሀገሪቱ እያቀረበ እንደሚገኝ ከፋብሪካው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓባይ የዘመናት ሃሳብ መቋጫ ፤ የታላቅ ሕዝብ መገለጫ”
Next articleውይይትን የችግሮች መፍቻ አይነተኛ መሳሪያ አድርጎ የመጠቀም ልምድን ማዳበር ተገቢ መኾኑን የሰሜን ሸዋ ዞን ገለጸ፡፡