
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ዜማ እያዜሙ መሸኘቱ ፣ ቅኔ እየተቀኙ መሰናበቱ ፣ ለዘመናት ያለማቋረጥ ሲጓዝ በስስት ማየቱ ያበቃ ይመስላል፡፡ ዓባይ ማደሪያ የለሽ ግንድ ይዞ ይዞራል ይሉት ነገር ተቀይሯል፡፡ ዓባይ ማደሪያውን አግኝቷል ፤ በእናቱ ቤት ባይተዋር ኾኖ መኖሩ ቀርቷልና፡፡ አሁን እርሱ ባለ ሀገር፣ ባለ አድባር፣ ማደሪያና ማረፊያ ያለው ኾኗል፡፡
ቅብዓ መንግሥት ተቀብተው ፣ በትረ መንግሥት ጨብጠው ፣ በወርቅና በአልማዝ ያጌጡ ዘውድ ጭነው፣ በእንቁ የተንቆጠቆጠ ካባ ደርበው፣ በታላቁ ዙፋን ላይ የነገሡ ነገሥታት አንድ ብርቱ ሃሳብ ነበራቸው-ዓባይን ባለሀገር ማድረግ፡፡ ነገሥታቱና ሕዝቡ ዓባይን በሀገሩ ያስቀሩት፣ ማደሪያና መሰንበቻ ያዘጋጁለት፣ አቅጣጫውን ቀይረው በሀገሩ ምድር ብቻ እንዲፈስስ ያደርጉት ዘንድ ሲያስቡ ኖረዋል፡፡
ዳሩ “ለሁሉም ዘመን አለው ፣ ከሰማይ በታችም ለኾነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው” እንደተባለ ጊዜው ይደርስ ዘንድ ግድ ነበርና ሀሳባቸውን ሳይተገብሩት፣ ዓባይንም በምድራቸው ማደሪያ ሳያዘጋጁለት አለፉ፡፡ ሃሳባቸው እና ታላቁ ውጥናቸው ግን ከኀያል ስማቸው ጋር ከመቃብር በላይ ኖረ፡፡ ለትውልድም ሲነገር እና ሲዘከር ዘለቀ፡፡ ዓባይ የኢትዮጵያን አፈር እያፈሰ በኢትዮጵያዊያን ቅኔና ዜማ እየታጀበ ሲፈስስ ኖረ፡፡
በኢትዮጵያ አብራክ የፈለቀው ዓባይ የግብጽን በረሃ እንዳረሰረሰው፣ ግብጻዊያንንም ከሥልጣኔ ላይ ሥልጣኔ እየደራረበላቸው ዘመናት አለፉ፡፡ የግብጽ ሥልጣኔዎች ዓባይን ተከትለው የፈለቁ ፤ ዓባይን ተከትለው የረቀቁ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዓባይን እንገድባለን ባሉ ጊዜ የግብጽ ሹማምንት ለኢትዮጵያዊያን ማሩን፣ ይቅር በሉን፣ በረሃብና በችግር አትፍጁን እያሉ ገጸ በረከቶችን እየያዙ በኢትዮጵያዊያን ነገሥታት ፊት እጅ ይነሳሉ፡፡ በእጅ መንሻና በልመናም የኢትዮጵያዊያንን ልብ ያለዝባሉ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ደግ ልብ ያላቸው ናቸውና ያዝኑላቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ከጀርባዋ አያሌ ሤራዎች ተሸርበውባታል፤ የክፋት ጦሮች ተሹለውባታል፣ የክፋት ሰይፍ ተስሎባታል፡፡ ዳሩ አብዝታ በምታምነው አምላክ እና በልጆቿ ብርታት ከጀርባ የተሸረቡትን የክፋት ጉንጉኖች እየበጣጠሰች ለዚህ ደረሰች፡፡ የዘመናት ሃሳቧን ተገበረች፣ የዘመናት ራዕዩዋን እውን አደረገች፣ የዘመናት ውጥኗን ሠርታ አሳየች፡፡ ዓባይ የዘመናት ሀሳብ መቋጫ፣ የታላቅ ሕዝብ መገለጫ ነው፡፡
ዓባይ ዛሬም በጨለማ የሚዳብሰውን ሕዝብ ብርሃን ያሳይ ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል። በችግር የኖረውን ከችግር ያላቅቅ ዘንድ ታምኖበታል፡፡ ለዓመታት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን የተገነባው የዓባይ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ተጠናቅቋል፡፡ ይህ ደግሞ ሃብታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን ለሰጡ፣ ተስፋም ለሰነቁበት ኢትዮጵያዊያን አስደሳች ነው፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የሚታወስበት መልካምም መጥፎም ትዝታዎች ይኖሩታል፤ የዚህ ዘመን ትውልድም በርካታ ፈተናዎች እና የሚታረሙ አካሄዶች ቢኖሩበትም በትውልድ የሚታወስ አንድ የጋራ አሻራ አኑሯል፡፡ ይህም ለዚህ ዘመን ትውልድ ታላቁ አሻራው፣ በአንድነት የሚያስጠራው ነው፡፡
አንጋፋው የጥበብ ሰው ጋሽ ደበበ እሸቱ ዓባይ ብዙ ፈተናዎችን አልፎ እውን የኾነ አኩሪ ታሪክ ነው ይላሉ፡፡ ቀኝ ገዢዎች ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛታቸው አንድ አካል ለማድረግ፣ ዓባይና ጣናንም ለእነርሱ ለመጠቀም ብዙ ወጥነው ነበር ነገር ግን ውጥናቸው ሳይሳካላቸው ቀረ ነው የሚሉት፡፡ የዓባይ ግድብ በኢትዮጵያዊያን ብርታትና በአምላክ ፈቃድ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡ በዓባይ ውኃ ሙሌት ያለምንም ልዩነት ኢትዮጵያዊ የኾነ ኹሉ ሊደሰትበት የሚገባ ጉዳይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ዓባይ ለኢትዮጵያ ብርሃን ከመኾን አልፎ ለጎረቤት ሀገርም ብርሃን የሚኾን፣ ለኢትዮጵያ ብርሃን እና ገንዘብ ይዞ የሚመጣ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የውኃ ሃብታም መኾናቸውን ያወቁበት ዘመን መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በዓባይ ግድብ የኾነው ኹሉ የሚያኮራ ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
ዓባይ አሁን ላይ የወደፊቱ የኢትዮጵያ እድገት መሠረት ኾኗል፤ ዓባይ አንድ ላይ የሚያሰባስበን ኀይል ነውም ብለዋል፡፡ የዓባይ ግድብ መሙላት አንድነትን የሚፈጥር መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በዓባይ ግድብ አንድ ግድብ ሳይኾን ሀገር ነው የተገነባው ያሉት ጋሽ ደበበ አሁን መነታረኩን አቁሞ ዓባይ የሚሰጠውን ጥቅም በጋራ መጠቀምና ሀገርን በጋራ ማልማት ይገባልም ነው ያሉት፡፡ ልናገኝ የሚገባንን ጉልበት ሁሉ በዓባይ አግኝተናል፣ አሁን ላይ መናቆሩን መተው አለብን፣ አሁን አንድ መኾን ይገባናል ነው ያሉት፡፡
መናቆር ከጉዳት በስተቀር የሚያመጣው ረብ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለውን መናቆር ትቶ ለትውልድ የሚጠቅም ሥራ ላይ ማተኮር እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ሀገርን እንገባ፣ አንድ እንሁን፣ መናቆራችን ይቅር፣ የምንሸሽባት ሳትኾን የምንሰባሰብባት ሀገር እንድትኾን እንሥራም ብለዋል ጋሽ ደበበ፡፡
የቀኝ ግዛት መንፈስ ያለቀቃቸው ሀገራት በዓድዋ ድል ዛሬም ቂም እንደቋጠሩ እንደኾነ የሚናገሩት ጋሽ ደበበ ኢትዮጵያዊያን የውስጥ አንድነታቸውን አጠናክረው የኢትዮጵያን ክብር የሚመጥን ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሀብቷን ከመጠቀም የሚከለክላት ሀገር የለም፡፡ የሌሎችን ሳትነካ የራሷን መጠቀም ትችላለችም ብለዋል፡፡ አበው ጊዜ ሲጠብቁለት የነበረው ሀሳብ ዛሬ ላይ ባለው ትውልድ መተግበሩንም ገልጸዋል፡፡
ከፊታችን የተሰጠን ማዕድ አለ፣ ይሄን ማዕድ የምንበላበት ዘመን ደግሞ ቀርቧል፤ ይሄን ማዕድ በጋራ ለመብላት በአንድነት መቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ከኢትዮጵያዊያን ቁጭ ብሎ በመነጋገር፣ ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ አንድ ላይ የምንቆምበትን መንገድ መፈለግ ያሻል ነው ያሉት፡፡ ሀገር የምትጸናበትን ነገር እንሥራም ብለዋል፡፡ ጥልና ጥላቻን እየተውን እውነተኛውን የኢትዮጵያን ታሪክ እያወሳን፣ እውነተኛ ነገርን በሀገር ላይ መሥራት ይገባናልም ብለዋል ጋሽ ደበበ እሸቱ፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!