“ገጠሩን ለማልማት ተደራርበን ሳይሆን አብረን፤ ተገፋፍተን ሳይሆን ተጠጋግተን እንሰራለን” ዶክተር ድረስ ሳህሉ

21

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የገጠር ልማት ዘርፍ ክላስተር መሥሪያ ቤቶች የጋራ ትውውቅ እና ለቀጣይ ጊዜያት የሥራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል ውይይት በባሕር ዳር ከተማ አካሂደዋል፡፡

ዘርፉ ሃሳብንና ሃብትን በጋራ ለመጠቀም፣ በአንድ ተግባር ላይ የተለያዩ ተቋማትን መደራረብ በመቀነስ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር፣ መገፋፋትን ለማስቀረት፣ የጋራ ግብን በተባበረ ኃይል ለመፈጸም፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ አሰራርን ለማስፈን በአንድ ተዋቅሯል ብለዋል፡፡

በቅርቡ በክልሉ የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ሥራ ተከትሎ የክልሉን አመራር እና አደረጃጀት ፈትሾ መስተካከሉ ይታወሳል፡፡ ይኽንን ተከትሎ በአራት ተከፋፍለው ከተደራጁት ክላስተሮች መካከል የገጠር ልማት ዘርፍ ክላስተር አንዱ ነው፡፡ ስድስት ተጠሪ ተቋማትን በአንድ አካትቶ የያዘው ግብርና ቢሮን ጨምሮ ውኃና ኢነርጂ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ መንገድ፣ ማዕድን እንዲሁም መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮዎች በአንድ የተሰባሰቡበት ክላስተሩ የትውውቅ እና በቀጣይ ጊዜያት ተግባራት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በሥራ ተፈጥሯቸው እና ተመጋጋቢነታቸው በአንድ ክላስተር የተደራጁት ተቋማት ገጠሩን ለማልማት እና ከተማውን ለመመገብ የሚያስችሉ ናቸው ያሉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኅላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ተቋማት በክላስተር ሲደራጁ ተደራጅተዋል ከማለት የዘለለ በጋራ ተነጋግሮ ወደ ተግባር መግባት የተለመደ አይደለም ያሉት ዶክተር ድረስ ከማደራጀት ባለፈ ተግባራዊ ትብብር እና ቅንጅት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ዶክተር ድረስ የግብርና ሥርዓቱን ማዘመን፣ ምርትና ምርታማነትን መጨመር፣ የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ማምረት፣ መስኖን ማስፋፋት፣ በክልሉ የሚገኘውን ማዕድን በአግባቡ አልምቶ ተጨማሪ የልማት አቅም ማድረግ እና የመንገድ ትስስሮችን ማጠናከር የክላስተሩ ቀዳሚ ዓላማ ነው ብለዋል፡፡

ተጠባቂውን ለውጥ ለማምጣት እና ገጠሩን ለማልማት “ተደራርበን ሳይሆን አብረን፤ ተገፋፍተን ሳይሆን ተጠጋግተን እንሰራለን” ያሉት የክላስተሩ አሥተባባሪ ወደ ተግባር የሚተረጎም ዕቅድ፣ ወጥ የሆነ የመረጃ ሥርዓት መገንባት እና ተቋማዊ ትስስርን ማጠናከር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ ተቋማዊ ባሕል ግንባታ፣ የኅላፊነት ስሜት መፍጠር እና ምርጥ የአፈጻጸም ተሞክሮዎችን ቀምሮ ማስፋት እንደሚያስፈልግም ተነስቷል፡፡

ተወያዮቹ በተቋማት መካከል ለአሰራር አመች ያልሆኑ መመሪያዎች፣ ደንቦች እና አሰራሮች ተፈትሸው መፍትሄ ሊፈለግላቸው ይገባል ብለዋል፡፡ ተቋማቱን በአንድ ክላስተር ሥር ማቋቋም ብቻውን በቂ አይደለም ያሉት ተወያዮቹ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል የክትትል እና ድጋፍ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በክልሉ ከተፈጠረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ እስካለበት መንደር ድረስ ወርዶ ለማገዝ የሚያስችል ሁኔታ የለም ያሉት ሰራተኞቹ የክረምት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በምርት እና ምርታማነት ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት መሙላት ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ከሕዝቡ ጋር በመወያየት እና በመነጋገር ወደ ነበረበት ለመመለስ ሊሰራ እንደሚገባም ተነስቷል፡፡ የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና መሰል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችም መፍትሄ እንደሚያስፈልጋቸው በተወያዮች ተነስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ስኬት ነው” ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ
Next article“ዓባይ የዘመናት ሃሳብ መቋጫ ፤ የታላቅ ሕዝብ መገለጫ”