
ባሕር ዳር: ጳጉሜ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ስኬት መኾኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ገለጹ።
ዶክተር ያዕቆብ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዳይጀመር በርካታ ጫናዎች ሲደረጉ እንደነበር በማንሳት ግድቡ ግንባታው ከተጀመረ በኋላም የነበሩ ፈተናዎችን ኢትዮጵያ በጽናት ማለፏን ተናግረዋል።
የግድቡ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት መጠናቀቅ የነበረውን ጫና ሙሉ በሙሉ የቀለበሰ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይም በዲፕሎማሲው መስክ ሰፊ ዘመቻ ሲደረግ እንደነበር በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ በያዘችው እቅድ መሰረት የግድቡን ውሃ ሙሌት በማጠናቀቅ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል አስመዝግባለች ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግል ጥቅም ይልቅ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም እና ለቀጣዩ ትውልድ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ያነሱት ዶክተር ያዕቆብ ይህንንም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማሳየቱን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያውያን ችግሮችን ተቋቁመው በጥሪታቸው እየገነቡት ያለው ይህ ግዙፍ የኀይል ማመንጫ ግድብ አሁን ፍሬው መታየት ጀምሯል ብለዋል።
የግድቡ ውኃ ሙሌት መጠናቀቅም የሕዝቡ የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የዕውቀት አስተዋጽኦና የጸሎት ትጋት ውጤት መኾኑን በአፅንኦት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁልጊዜም የውኃ ሃብቶቿን ለማልማት ስታቅድ ጎረቤት ሀገራትን እና የታችኛው ተፋሰስን የጋራ ልማት ታሳቢ በማድረግ መኾኑን ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌትም በቂ ውኃ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲያልፍ በማድረግ መከናወኑን አንስተዋል።
አራተኛውና የመጨረሻው የውኃ ሙሌትም ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በቂ የውኃ መጠን እንዲያልፍ በማድረግ መከናወኑን ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ አብዛኛዎቹ ወንዞቿ ድንበር ተሻጋሪ መኾናቸው ለጎረቤት ሀገራትም ትልቅ ጸጋ ነው ያሉት ዶክተር ያዕቆብ ሆኖም አንዳንድ ሀገራት ሉዓላዊ መብቷን ለመገደብ ሲሞክሩ ይስተዋላል ብለዋል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብትን የመጠቀም መብት እንዳላት በሚገባ መገንዘግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብትን በፍትሐዊነትና በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የመጠቀም መርህን ይዛ እየተንቀሳቀሰች መኾኑን አረጋግጠዋል።
በቀጣይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮችም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና የወደፊቱን ትውልድ የልማት መብት የሚያስከብር ስምምነት እንዲኖር በጥንቃቄ መሥራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!