“በአዲሱ ዓመት ሁሉም ሰው ተስፋ ሊሠንቅ ይገባል” መምህር ጥቁኄር ወርቄ

21

ባሕር ዳር: ጳጉሜ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ተስፋ የሰው ልጅ ወደ ፊት ይኾንልኛል ይደረግልኛል፤ እኾናለሁ፣ አደርገዋለሁ ብሎ የሚመኘው ነገር ነው ብለዋል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን የቅኔና የአዲስ ኪዳን ትርጓሜ የትሩፋት አገልጋዩ መምህር ጥቁኄር ወርቄ።

አዲስ ዓመት ሲመጣ ተስፋ አብሮ ይመጣል የሚሉት መምህሩ ሰው ሁሉ በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ በመሰነቅ እናቅዳለን ነው ያሉት፡፡ የሰው ልጅ ባለፈው ዓመት የወጠነው ከቀናው በድል ያጠናቅቃል ያልቀናው እንደነገሩ አጠናቅቆ አዲስ ዓመት ሲመጣ በአዲስ መንፈስ አዲስ ተስፋን ይሠንቃል ብለዋል፡፡

“ገበሬ ንጹሕ ዘር በእርሻው ላይ ሲዘራ በቅሎ፣ አብቦ፣ አፍርቶ፣ የተሻለ እና ከዚያ የበለጠ ምርት ይሠጠናል ብሎ አስቦ ነው፡፡ እኛም አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ነገር እናገኛለን ሰላም ይመጣል አንድነት ይሰበካል፣ አብሮ መኖር ይታወጃል ብለን ተስፋ ማድረግ አለብን ነው ያሉት፡፡

መምህር ጥቁኄር ስለተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ300 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል ይላሉ፡፡ በመጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ 5 ከቁጥር 16 ላይ “ለምስኪኑም ተስፋ አለው” ይላል፡፡ ይኽ ኀይለ-ቃል የሰው እጅ አይተው የሚኖሩ ምስኪኖች የራሳቸው የኾነ ተስፋ እንዳላቸው ያመላክታል ይላሉ፡፡ ያለተስፋ የሚኖር ግዑዝ ነው ብለዋል፡፡ ማንኛውም ሰው ተስፋ ሊኖረው ተስፋ ሊሰንቅ ይገባል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

በመጽሐፈ እዮብ ምዕራፍ 6 ቁጥር 76 “ተስፋ የሌለው ሰው ንግግሩ እንደነፋስ ነው” ይላል ያሉት መምህሩ ነፋስ አይጨበጥም ተስፋ የሌለው ሰው ንግግርም አይጨበጥም ብለዋል፡፡ በማንኛውም ቦታ የሚኖርና በየትኛውም ሁኔታ ላይ ያለ ሰው ተስፋ ሊኖረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ሮሜ 12 ከቁጥር 12 ላይ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፣ በጸሎት ጽኑ ፤ በመከራ ታገሱ ይላል ፤ የሰው ልጅም ምንም ዓይነት መከራ ቢገጥመው ያ መከራ የሚያልፍ ነው እና ተስፋ ማድረግ አለበት ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ተስፋ ያደረገ ሰው ከታመመ ይፈወሳል፣ ካጣ ያገኛል ፣ ከራበው ይጠግባል፣ ከተራቆተ ይለብሳል፣ ከደከመው ይበረታል ነው ያሉት፡፡ የማይነጋ ሌሊት የለም እና በአዲሱ ዓመት ሁሉም ሰው ተስፋ ሊሠንቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

አዲሱ ዓመት የሰላም የብልጽግና እና ሁሉም በፍቅር የሚኖርበት ዓመት እንዲኾን መምህር ጥቁኄር ተመኝተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሁሉም ሰው መጭውን አዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ መቀበል አለበት” ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም
Next article“የህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን በመቋቋም ያስመዘገበችው ስኬት ነው” ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ