“ሁሉም ሰው መጭውን አዲስ ዓመት በአዲስ ተስፋ መቀበል አለበት” ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም

34

ባሕር ዳር: ጳጉሜ 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ ዓመት ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ እንደሚመጣ ሰው ተስፋ ማድረግ አለበት ይላሉ በአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የዳዕዋና የትምህርት ዘርፍ ኀላፊ ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም፡፡

ሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም ለኹሉም እምነት ተከታዮች አዲስ ዓመት የሰላም የእድገት እና በፍቅር የሚኖርበት ዓመት እንዲኾን ተመኝተዋል፡፡

“በኢትዮጵያ መስከረም ሲጠባ አዲስ ዓመት መጣ ብለን በደስታ እንቀበላለን” ብለዋል፡፡ አዲሱን ዓመት ስንቀበል በአዲስ መንፈስ ፣ በአዲስ አስተሳሰብ በአዲስ አመለካከት መቀበል እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት ኹሉም በእኩልነት ፣ በአንድነት እና በመከባበር የሚኖርባት ሀገር ትኾናለች ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል፡፡ ይህ የምንናፍቀውን መልካም ተስፋ እንዲጸና እና ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ተስፋ የሚለው ቃል በችግር ውስጥ እንኳን ቢኾን በአምላኩ ላይ ተስፋ ማድረግ እንዳለበት ያስተምራል ይላሉ ሼህ ሙሐመድ፡፡

ፈጣሪ አዲስ ነገር ያምጣልኝ ብሎ ማሰብ አለበት ብለዋል፡፡ ተስፋ ያልቆረጠ አስተሳሰብ ይዞ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ይገባል ያሉት ሼህ ሙሐመድ ተስፋ መቁረጥ የደካሞች እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡ ተስፋ የማይቆርጥ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ወደ ኋላ ያለውን ትቶ ወደፊት ያለውን ጥሩ ነገር ተመልክቶ ተስፋ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አብሮነት እንዲጎለብት ሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋገጡ።
Next article“በአዲሱ ዓመት ሁሉም ሰው ተስፋ ሊሠንቅ ይገባል” መምህር ጥቁኄር ወርቄ