“ልጆቼ ሆይ እንደታጨደው ሳር አትሁኑ! ገና እንደሚበቅለው እንደለመለመው ሁኑ እንጂ።” የጋሞ አባቶች

634

ከደቡብ ጫፍ እስከ ሰሜን ጫፍ የፍቅር ዥረት ፈስሷል። ሕዝቡ ሁሉ በፍቅር ዥረት አንጀቱ ርሷል። የኢትዮጵያዊያን ፍቅር ለይስሙላ አይደለም።

ከልብ የመነጨ እንጂ። በምንጮቿ ብዛት የተነሳ አርባ ምንጭ ከተባለችው ከፍቅር ከተማዋ ከጋሞዎች ምድር የተነሱት የፀብ እሳት አብራጅ ውሃዎች፣ የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች ወደ ሌላኛው የፍቅር መገኛ አማራ ምድር ገብተዋል። ደጉ የአማራ ሕዝብም ቅኖቹን እንግዶች በየመንገዱ ቄጠማ እየነሰነሰ፣ ከሚበላው እያጎረሰ፣ በባሕል ሸማ እያላበሰ በየመንገዱ እየተቀበለ ሸኝቷቸዋል። አማራ ለወዳጁ ፈትፍቶ ያጎርሳል፣አቅፎ ያንተርሳል፣ጥበብ ሸማውን ያለብሳልና። እንደ ዐይኑ ብሌን እየሳሳም እንግዳውን ቤቱ ያለ ያህል እዲሰማው ደርጋልና፡፡ ይህ የሕዝቡ መልካም እና ዘመን ተሻጋሪ እሴት ነው፡፡

የጋሞ ሽማግሌዎች ትናንት ስለፍቅር ተንበረከኩ፣ የተደገሰውን የፀብ ድግስም ተጠጥቶ ሳያሳከር፣ ተበልቶ ሳይመርዝ በእጃቸው በያዙት ለምለም ሳር አከሸፉት። ኢትዮጵያዊያንም ስለሽማግሌዎቹ ብዙ ነገር አሉ። ጉዳዩ ለትውልዱ አዲስ ሆኖ እንጂ ይሄስ በቅርብ የመጣ ስርዓት አልነበረም። ከቀደሙት የቀደመ ነው። የሀገርና የወገንን በሽታ ያከመ ጥንታዊ ነው የጋሞ የሽምግልና ስርዓት። ከጋሞዎች ጋር አብሮ የተፈጠረ እንደሆነም ይነገርለታል።

ዓለም ያየውን ሁሉ ኢትዮጵያውያን አስቀድመው አይተውታል። ደራሲያን፣ ፀኃፈ ተውኔት፣ ገጣሚያን፣ ዘማሪያን፣ ዘፋኞች… ሁሉም በየሙያቸው ስለኢትዮጵያ ተናግረዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከተነገረው ታሪኳ ይልቅ ያልተነገረው ይልቃልና

“ጥንትም ላያልቅላት ምድሩ ላይነካ፣

ስትጨልፍ ዋለች ዓባይን በማንካ::”

እንዳሉት የኢትዮጵያ ታሪክ ተቀመሰ እንጂ አልታዬም። ተጀመረ እንጂ አልተጨረሰም።

በኢትዮጵያ ምድር በደቡቡ ንፍቅ በኩል ስማቸው ብዙ፣ ዝናቸው ግሩም፣ ፍቅራቸው ውብና ድንቅ የሆኑ ሕዝቦች ይገኛሉ። ፈጣሪ ልሳናቸውን አብዝቶ ያሳመራቸው እኒያ ደግ ሕዝቦች በየልሳናቸው እየተናገሩ እንግዳን ሲቀበሉ ልብን በፍቅር ይሰብራሉ። በደቡብ ንፍቅ የሚገኙት አኒያ ደግ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ባሕል፣ ወግ፣ እሴትና ማንነት ማሳያ ሙዚዬሞች ናቸው። በዚያ ምድር አንድ እልፍ እንደተጓዙ ሌላ ቋንቋ፣ ሌላ ብሔር፣ ሌላ ወግና ልምድ ይገኛል።

ከ56 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚገኙበት የሚነገረው ይሄው አካባቢ ድንቅ ነገሮችን በጉያው አቅፏል። የጋሞ ሕዝብ ከእነዚህ ድንቅ ሕዝቦች መካከል የሚገኝ ነው። ከኦሞቲክ የቋንቋ ቤተሰብ የሚመዘዘውን ጋሞኛ ቋንቋውን እየተናገረ፣ ባሕልና እሴቱን በስርዓት እየሰደረ፣ ዘመንን አሳልፎ ሌላ ዘመን እየተሻገረ ፍቅርን፣ ሰላምንና አንድነትን እያስተማረ የኖረ፣ እየኖረ ያለ፣ የሚኖር ሕዝብ ነው። ጋሞዎች ትናንት መከራ ሲመጣ ተንበረከኩ፣ በጉልበታቸው እየዳሁም ፍቅርን፣ አንድነትንና ሰላምን ሰበኩ፣ ያን የመከራ ቀን አሳልፈው ቀና ብለው ተራመዱ።

ምክር ቤት ሳይፈጠር፣ ክልልና ዞን ሳይከፈል፣ ድንቅ ስርዓት በጋሞች ዘንድ ነበር። ጋሞ በቀድሞው በጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት ስር የነበረ፣ ቆይቶ በጋሞ ጎፋ ዞን ስር የነበረ፣ በቅርብ ደግሞ ራሱን ችሎ የጋሞ ዞን የሆነ ነው። ከጋሞ አባቶችና ወጣቶች የአብሮነትና የሰላም ጉዞ ተሰታፊው አቶ ዘነበ በየነ እንደነገሩኝ በጋሞ ውስጥ ከ300 በላይ ጎሳዎች ይገኛሉ። “ባልና ሚስት ካልተጋጨ, ድንጋይና ድንጋይ ካልተፋጨ ምኑን ተኖረው” እንደሚሉት አበው በሕይወት ውስጥ ግጭት አይጠፋም። ከፀብ ማግስት ፍቅር ይጠነክራል፤ከወጊያ ማግስት ጠላት ይፈራል፡፡ እንደሚባለው ሁሉ ፀብ በሰላማዊ መንገድ ሲፈታ ቂም አይኖረውም።

ጋሞዎች ባልና ሚስት፣ጎረቤት ከጎረቤት ማሕበረሰብ ከማሕበረሰብ ጋር ሲጣላ የሚፈቱበት ዘመን የተሻገረ ባሕላዊ ስርዓት አላቸው። ይህን ስርዓትም “ወጋ ኦጋ” ይሉታል። በዚህ ስርዓት የማይፈታ ችግር፣ የማይወርድ ዕርቅ የለም። ሁሉም ችግር ከዚህ ስርዓት በታች ነው። የወንጀልም ይሁን የፍትሀብሔር ጉዳዮች በዚህ ባሕላዊ ስርዓት በአጭር ጊዜ፣ በትንሽ ጉልበት ይፈታሉ። በዚህ የዕርቅ ስነ ስርዓት በዳይ፣ ተበዳይ ተገናኝተው ጉዳያቸውን ያስረዳሉ። የአካባቢው ሽማግሌዎችም ቂም በሚሽር መልኩ ያስታርቋቸዋል።

ከጋሞ የሽምግልና ስርዓት አንደኛው ቱጌይባላል። ቱጌ ማለት ያልታሰበ ችግር ወይንም ግጭት ሲፈጠር የሚፈታበት የሽምግልና ስነ ስርዓት ነው። ባሳለፍነው ዓመት የጋሞ አባቶች እንዳደረጉት ሁሉ ድንገተኛ ግጭት ሲነሳ የጋሞ አባቶች ለምለም ሳር በእጃቸው ይዘው ከፊት ለፊት ይቆማሉ። የሽምግልና ስርዓቱም ከፊት መቆም ነው። ሽማግሌዎቹ ከፊት ለፊት ቆመው ፀቡ ካልበረደ ተንበርክከው ይለምናሉ። ፀቡን በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈቱ ቃል ይገባሉ። በዚህ ሰዓት አባቶቹን የሚያልፍ አንድም ሰው አይኖርም። እናቶች ደግሞ በዚህ ድንገተኛ ግጭት ጊዜ መቀነታቸውን ፈትተው ጡታቸውን በመያዝ ፀብ እንዳይኖር ሰላም እንዲሰፍን ይለምናሉ። ፀቡ ከጠና ከተጋጩት መካከል ይተኛሉ። እናቶችን “ማሪዣም” ይሏቸዋል። ማርያም እንደ ማለት ነው። እናቶችም ፀብ ሲመጣ “እኔን ውሰዱ እኔ ማርያም ነኝ፤ ማርያምን ረግጦ መሄድ አይቻልም አትጋጩ”  በማለት ይማፀናሉ። ከዚህ በኃላ ማንም ለበቀል የተዘጋጀ እጅ ቢመጣ ክንዱን ለበቀል አይዘረጋም። ይህን ቢያደርግ “ጎሜ” ነው። ጎሜ ማለት ሀጥያት፣ እርግማን ማለት ነው። የእናቶችና የአባቶች እርግማን ይደርሳል ተብሎ ስለሚታሰብ ጎሜን ደፍሮ የሚፈፅም የለም።

በጋሞ ብሔረሰብ ውስጥ ያልተጠበቀ ግጭት ሲፈጠር ሕዝብ የሚቀሰቀሰው “ኡሎ አላ! ኡሎ አላ”  በሚል ጥሪ ነው። ሕዝቡም ይሰበሳባል። ግጭቱ የሁለት ወገኖች ሆኖ የከፋ እንደሆነ የፀብ ማብረጃ በሬ ወይም ላም ይቆማል። የጀግንነት ምልክት የሆነው የነብርና የአንበሳ ቆዳም ይለበሳል። በሬውን አልፎ ፀብ የሚፈፅም የለም። ጎሜ በጋሞ ብሔረሰብ ዘንድ የመጥፎ ሥራ ክፍያ እንደሆነ ይነገራል። ወግና ስርዓቱን በመጣስ ጎሜ የፈፀመ ሰው በሀብቱ፣ በቤቱ እና በልጆቹ ላይ ቁጣ እና ቅጣት ይወርድበታል ይባላል። ሽማግሌዎችንና እናቶችን ተላልፎ ጎሜ የፈፀመ ከማሕበረሰቡ ይገለላል።

አባቶች የሚይዙት ሳር ምክንያት አለው፡፡ ሰው እንደታጨደ ሳር መሆን የለበትም እንደሚበቅል እንጂ ለማለት ነው። አነርሱም “ልጆቼ ሆይ እንደታጨደው ሳር አትሁኑ፤ ገና እንደሚበቅለው እንደለመለመው ሁኑ እንጂ” እያሉ ነው የሚለምኗቸው። ቱጌውን የሚያቆሙት አባቶች አንደ ስልጣን ተዋረዳቸው ኦጋዴ፣ጋና፣ ካሬ ወዘተ እየተባሉ ይጠራሉ። የሁሉም ገዢ ደግሞ “ካኦ”  ይባላል፤ ንጉሥ እንደማለት ነው።

በጋሞ ብሔረሰብ 42 ደሬዎች (የተለያዬ ስም ያላቸው ማኅበረሰቦች) እንዳሉ ይነገራል። ደሬዎችም የራሳቸው ድንበር አላቸው። አንዱ የአንደኛውን ላለመንካት በመሀላ ቃል የታሰረ ነው። መሃላው “ጫቆ” ይባላል። ቢጋጩ እንኳን ለመዳኜት አስቀድመው ቃል ይገባሉ። በድንገተኛ ግጭት ሞት ቢኖር በአጭር ቀን እርቅ ይፈፀማል። እርቅ ሲፈፀምም የሟችና የገዳይ ቤተሰቦች አብረው በመብላትና በመጠጣት ነው። ይህም ሰነ ስርዓት “ጎምታ” ይባላል። የእርቅ እርድ ሲፈፀም እርዱን የሚፈፅመው “ማካ” ይባላል። ማካ ማለት ባህላዊ የጋሞ ቄስ ነው። ከታረደ በኃላ “ኮይራፍሬ” ወይም የጎሳ መሪው ከሟችና ከገዳይ ጎሳ መሪዎች ጋር በመሆን ደም እና ፈርሱን በመርገጥ ሦስት ጊዜ ዮ….ዮ….ዮ….በማለት ጎማታ አውርደው ምግቡን በጋራ ይመገባሉ።

ዮ….ማለት ሰላም አውርደናል፤ እርቅ አድርገናል ማለት ነው። ከዚህ በኋላም ቂምና በቀል የለም፤ ጉዳዮ በእርቅ ተሽሯልና።

ፀቡ የጎሳ ከሆነ ደግሞ ለሰባት ተከተታይ ዓመታት ይሄው ስርዓት ይፈፀማል። ግጭቱ ከጎሳ ውጭ ከሆነ ግን “ኦጋዴዎች”  (ባህላዊ ዲፕሎማቶች) ከማካ (ከባህላዊ ቄሱ) ጋር በመሆን እርቁን በአንድ ጊዜ ይጨርሳሉ። በጋሞ ብሔረሰብ ውስጥ አስደናቂ ባህል፣ ወግና ትውፊት አለ። ጋሞዎች ያርሳሉ፣ ከብት ያረባሉ፣ የሽምና ሥራም ይሠራሉ። ሽመና የተከበረ ሙያ ነው። እነዚያን የሚያማምሩ ልብሶቻቸውን የሚሰሯቸውም በሽመና ነው። በጋሞዎች ከጣትም ጣት ይበልጣል፤ ከሰውም ሰው ይበልጣል፤ ይህም ይከበራል፤ የሚል ትልቅ ህግ አላቸው። እናም ሽማግሌዎችና ታላላቅ ሰዎች ይከበራሉ። ለምን ካሉ መካሪ ናቸውና። መከባባር፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ ሰላምና አርቆ አስታዋይነት የጋሞዎች ከደም ጋር የተዋሃዱ ህጎች ናቸው። በጋሞዎች አሁን ዘመኑ የምክር ቤት አባላት እንደሚሏቸው ሁሉ ከጥንት የነበሩ ባህላዊ “ዲቡሻዎች” አሏቸው። ዲቡሻዎች የሕዝቡን ችግር እየተከታተሉ የሚፈቱ ናቸው። በሀገር ላይ ጦርነት የሚያዘምት ነገር ከመጣም በ‹‹ካኦ›› አማካኝነት ዘመቻ ይታዘዛል። ሕዝቡም ይዘምታል። ይህ ህግ ነው።

እኝህ የጋሞ አባቶች ሰላምና ፍቅር፣ አብሮነትና አንድነት ስንቅ አድርገው መዳረሻቸውን ጎንደር ለማድረግ ጉዞ ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል። በጉዟቸው አዲስ አበባ ቤተ መንግስት ገብተው ስለሰላም መክረዋል። መልካም አሸኛኘት ተደርጎላቸውም በርካታ ኪሎ ሜትሮችን እያቆራረጡ “መልክ አልታየም እንጂ ቢታይማ ኑሮ፣ ባሕር ዳር ነበረች የሁሉም ወይዘሮ” ከተባለላት ውብ ከተማ ትናንት ጥር 8/2012 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ገብተዋል። ባሕር ዳር ሲገቡም የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነን ጨምሮ የከተማ አስተዳድሩ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በአቀባበል ስነ ስርዓቱ የጋሞ አባቶች  እንዲህ መክረዋል፡፡ “የኢትዮጵያን ፀጋ ለመጠቀም ሰላምን ማስቀደም አለብን። ኢትዮጵያውያን መለያዬት እንዳንችል ሆኖ በጋራ የተሸመንን ሕዝቦች ነን። ለኢትዮጵያውያን ፍቅር፣ደስታ፣ አንድነትና መከባበር እንጂ ፀብ አያምርብንም። ይህን የፈተና ዘመን በጋራ እንለፈው” ነው ያሉት።

ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ደግሞ “እናንተ አባቶች ትናንት ታሪካዊ ሥራ ሰርታችሁ አኩርታችሁናል፣ ዛሬም እናንተን ይዘን የማናልፈው ችግር የለም” በማለት አድናቆት እና ተስፋቸውን ተንግረዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ፍቅር አዋቂ፣ ታታሪና ሰው ወዳጅ ነው፤ ሀገሩም፣ ሰውም የእናንተ ነው ብለዋቸዋል። “የአማራ ሕዝብ ባልዋለበት፣ ባልሥራውና ባላሰበው የሀሰት ትርክት ታሪኩ እንዲጎድፍ፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር መቃቃር እንዲፈጥር ሲደረግ የቆዬ ተበዳይ ሕዝብ እንደሆነ ያስታወሱት ዶክተር ሙሉቀን፣ ይህን መልካም ሕዝብ በዐይናችሁ አይታችሁ ከፍቅሩ ተካፍላችሁ ለመሄድ ስለመጣችሁ ደስ ብሎናል፣ እናንተም ደስታን ታገኛላችሁ” ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ መላ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን የሚታትር ቀን እና ሌሊት ፀሎት ሳያስታጉል ሰላምና ፍቅር የሚለምን ሕዝብ ነውም ብለዋል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም በጋራ በመሆን የምታስቀና ኢትዮጵያን መገንባት እንዳለበት ነው ዶክተር ሙሉቀን ያሳሰቡት። የጋሞ አባቶችና ወጣቶች የአብሮነትና የሰላም ልዑካን ዛሬ ቅዳሜ ዐባይን ተሻግረው፣ ጣናን ወደጎን ትተው፣መልካሙን የጎንደርን ምድር እየቃኙ ከመናገሻዋ፣ ከእነርሱም መዳረሻ ጎንደር እንደሚገቡ ይጠበቃል። በጎንደር ቆይታቸውም። የጥምቀት በዓልን ይታደማሉ፡፡ የእነ ፋሲል ሀገር እምዬ ጎንደርም ቄጤማ ጎዝጉዛ፣ እልፍኟን አሳምራ፣ ካባውን ደርባ እንግዶቿን ትቀበላለች፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!፤ ፍቅር ለህዝቦቿ!

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

Previous article“የጢንዚዛ ገንዳዎችን ለማሠራት እስከ 30 ሚሊዮን ብር ተጠይቀናል::” ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
Next articleየፋሲለደስ ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪዎች በ20 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ክፍሎችን ሊያስገነቡ ነው፡፡