በዕቅድ የሚመራ ሕይወት ለስኬት የታጨ ነው!

24

ባሕር ዳር: ጳጉሜን 06/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሰው ልጅ ከእለት እስከ ሕይወት ዘመኑ ስኬት ላይ ለመድረስ የዘመን ትግል ያደርጋል፡፡ የስኬት መሰረቱ ደግሞ ዕቅድ እንደኾነ ይታመናል፡፡ እናም እያንዳንዱ ባለ ርዕይ ሰው ለፍላጎትና ምኞቱ ስኬት፣ለሕይወት ዘመኑ ደማቅ አሻራ ያቅዳል፣በዕቅዱ መሰረትም ይተገብራል፡፡

የዕቅድ መቼቱ እንደ ጉዳዩ የሚወሰን ቢኾንም በተለይ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሰው ልጅ የሕይወት መንገድ የፍላጎትና ምኞት ማሳኪያ በጎ አሻራ ለማስቀመጥ ትልቁ መንገድ የአዲስ ዓመት አዲስ ዕቅድ ነው ይባላል፡፡

በአዲስ ዓመት አዲስ ዕቅድ በግል ሕይወት ስኬት ላይ ለመድረስ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ፣በየአንዳንዱ ግለሰብ ዘንድ ማቀድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡

የአዲስ ዓመት አዲስነቱ ፣ ለዕቅድ መሰረትነቱስ የባሕል ሚና እንዴት ይገለጻል፣ ዕቅድስ ከባሕል አንጻር እንዴት ይበየናል፣ ዕቅድን ለስኬት ለማብቃትስ የትኛው ስልት ይመከራል መቆያችን ነው፡፡ለዚህም የባለሙያ ማብራሪያን ይዘናል፡፡

ዶክተር ሞገስ ሚካኤል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር ናቸው፡፡ መምህሩ እንደሚሉት ዕቅድ የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር በሕይወት ዘመኑ ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቹን ለማሳካት የሚነድፈው የስኬት መስመር ነው፡፡ የትኛውን ጉዳይ እንዴት ፣የትና መቼ ጀምሮ ማሳካት እንደሚችል የጊዜ ፣የገንዘብ ፣የጉልበት የበጀት ልኬት ያስቀምጣል፡፡ በአብዛኛው ለስኬት መዳረሻ መንገዱም የአዲስ ዓመት አዲስ ዕቅዱ ስለመኾኑ ነው የሚያስረዱት፡፡ ሲጀመር አዲስ ዓመትን አዲስ የሚያስብሉት ባሕል ፣ተፈጥሮና ሃይማኖት ናቸው ይላሉ፡፡ እናም የአዲስ ዓመት ዕቅድ ከዚህ የተቀዳ ይኾናል ነው ነገሩ፡፡

በሰው ሕይወት ውስጥ ስኬትም ውድቀትም ፣አስፈሪም ፣አስደሳች ፣አስጊም የተስፋ ጊዜ ይፈራረቃል፡፡ ዶክተር ሞገስ እንደሚሉት የአዲስ ዓመት መሰረቱ ክረምት ነው ፣ ክረምት ወንዞች የሚሞሉበት ፣ በረዶና መብረቅ የሚፈራረቅበት፣ አራዊት የሚበረቱበት፣ ድግስና የደስታ ጨዋታው የሚገታበት ፣ የሰው ልጅ ማኅበራዊ ግንኙነትም በወቅቱ አስቸጋሪነት የሚገታበት ወቅት ነው፡፡

እናም ከክፉ ነገር መታደግን በመሻት ፈጣሪን መለመን በእጅጉ ይተገበራል፡፡ ወደ መስከረም ወር መጠጋት ደግሞ የምሥጋና ወቅት ይኾናል፡፡ ተስፋ እየታዬ አዲስ ሕልም እየተነደፈ አምላክ የሚመሰገንበት ነው ይላሉ ዶክተር ሞገስ፡፡አዲስ ዓመት በአካልና በመንፈስ ጸድቶ መታየትን የሚፈልግ ነው ፣በአዲስ ዓመት አዲስ መንፈስ አዲስ ዕቅድ ይነደፋል፡፡

በእርግጥም ከባሕልም ፣ከሃማኖትና ከተፈጥሯዊ ሁነት የተቀዱት ሥነ ቃሎቻችን ሁነት ዘጋቢነት መስክር ናቸው፡፡

“የዘንድሮን ክረምት አለፍነው በመላ፤
በትንሽ እንጀራ ጎመን ተቆልላ” ያለ ግለሰብ
የገንፎ ድስት ግባ የጎመን ድስት ውጣ ይላል፡፡
እሱም፤ “አትኩራ ገብስ ጎመን ባወጣው ነፍስ” እያለ ይወጣል፡፡
” ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት
ዶሮ ከጮኽ የለም ሌሊት”
እያለ ባሕላዊና መንፈሳዊ ሁነቱን እያቀናጀ የተስፋና የደስታ መንገዱን ያሰማምራል፡፡
በባሕላዊም ፣በሃይማኖትም የተፈጥሮ ለውጥ መነሻ በማድረግ አዲስ ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሸጋገሪያ ጊዜ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ወንዞች ይጎድላሉ፣ጋራ ሸንተረሮች ውብ ይኾናል፣ የአዝእርት ጸጋውም መንፈስን ያድሳል ፣ጥጋብን ያበስራል፡፡
“እሰይ መስከረም ጠባ ቅዱስ ዮሐንስ
አሮጌውን ጥለን አዲስ ልንለብስ” ብሎ ይቀኛል፡፡

እናም የብርሃናማው ወቅት የአዲስ ተስፋ ፣የአዲስ ስኬት መነሻ ለአዲስ ዕቅድ ምክንያት ለመኾን በቅቷል፡፡ ዕቅድን ለስኬት ለማብቃት የሚታይ ፣የሚደረስበት፣አቅምንና ጊዜን ያገናዘበ ማድረግ መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ ዶክተር ሞገስ በአጽንኦት የሚመክሩት ትልቁ ቁም ነገር አዲስ ዕቅድንና አዲስ ዓመትን በይቅርታ መጀመር ይገባል፡፡ ባሕሉም ፣ ሃይማኖቱም እንደሚያሰገነዝበው ከሰው እስከ ፈጣሪ ይቅርታ ትልቅ ዋጋ አለው ነው የሚሉት፡፡ መጥፎን መተው መልካሙን ማዳበር ፤ ይዞ መዝለቅ፣ ካለፈው በመማር ስህተትን ማረም ለዕቅድ ስኬት መሰረት ነው፡፡

የተዛባ አመለካከት ፣የተሳሳተ መንገድን ይዞ በአዲስ ዓመት አዲስ ዕቅድ ላይ ለመድረስን መሻት “ቂም ይዞ ጸሎት፣ሳል ይዞ ስርቆት” አይነት ነገር እንደማለት ይኾናል ነው ያሉት፡፡ በጎ አሻራ ለማስቀመጥ በጎ ተግባቦትና ግንኙነት ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ለሌላው ዕቅድ ስኬት ጉልበት እንጂ እንቅፋት መኾን አይገባውም፡፡ ክፉ እያሰቡ ለዕቅድ ስኬት የሚተባበር አይኖርምና ለስኬታችን ደጋፊ ለማብዛት በጎ መኾን ያስፈልጋል ምክራቸው ነው፡፡

እያንዳንዱ ያለፈ ጥፋትና ስህተት ተወግዞ ብቻ ማለፍ የለበትም ፣ለቀጣይ አዲስ የዕቅድ ስኬት ትምህርት መኾን አለበት ነው የሚሉት፡፡ እናም መስከረም ለኢትዮጵያዊያን የአዲስ ተስፋ ስንቅ ፣የአዲስ ዕቅድ መሰረት ነው፡፡ መምህሩ እንዳሉት በዕቅድ የሚመራ ሕይወት ለስኬት የታጨ ነውና ዕቅዳችንን በቅንነት ፣በንጽህናና በይቅርታ ማስመር ተገቢ ይኾናል፡፡

አዲሱ ዓመት፦ አዲስ አብሮነት፣ አዲስ ሰላም፣ አዲስ ቸርነትና ተስፋ ይዘህ ና መስከረም !

በጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኽምጠ ዊከ ጋዜጠ ንኻሽ 30/2015 ዓ.ስ
Next article“የአብሮነት ቀን ሲከበር የጋራ እሴቶችን በማጽናትና በማስቀጠል ሊኾን ይገባል” የባሕልና የስፖርት ሚኒስቴር