“የጢንዚዛ ገንዳዎችን ለማሠራት እስከ 30 ሚሊዮን ብር ተጠይቀናል::” ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

226

240 ጢንዚዛዎች ወደ ዓባይ ወንዝ ለሙከራ እንዲገቡ መደረጉን ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡

በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን እምቦጭ አረም በስነ ሕይወታዊ ዘዴ ለመከላከል ታስቦ የዛሬ ሦስት ዓመት ተኩል አካባቢ ከወንጂ መተሃራ ጢንዚዛዎች እንዲመጡ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ወደ ሥራ አልገቡም፡፡ ጢንዚዛዎቹን ያስመጧቸውም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የክልሉ አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን ናቸው፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጢንዚዛዎች ተንከባካቢ አቶ መላኩ አደራው አንድ ጢንዚዛ በቀን አምስት እንቁላሎችን እንደምትጥልና የቆይታ ጊዜያቸውም ከሦስት እስከ አራት ወራት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የእድገት ጊዜያቸውን በቶሎ እየጨረሱ ስለሚሞቱ በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና እምቦጭን በስነ ህይወታዊ ዘዴ የመከላከል አስተባባሪ ጌታቸው በነበሩ (ዶክተር) ጢንዚዛዎቹ እስካሁን ወደ ሥራ እንዲገቡ ቢደረግ ኖሮ በጥናት የተለዩት ሻሃ፣ ጣና ቂርቆስ፣ አግር ቅርኛ እና ጎርጎራ አካባቢዎች ላይ ያለውን እምቦጭ አረም ማስወገድ ይችሉ ነበር ብለዋል፡፡

አረሙን ለመከላከል በሚል ባዕድ ነገር ወደ ጣና ሐይቅ ለማስገባት በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ ማግኘት ስለሚገባ በታሰበው ጊዜ ወደ ሥራውን መጀመር እንዳልተቻለም ነው የተናገሩት፡፡ በቅርቡ ግን መረጃዎችን በማሟላት ፈቃድ ስለተገኘ ወደ ሥራ ለማስገባት 240 ጢንዚዛዎች ወደ ዓባይ ወንዝ ለሙከራ እንዲገቡ መደረጉን ዶክተር ጌታቸው ተናግረዋል፡፡ ሙከራው ስኬታማ መሆኑ ታይቶ ደግሞ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወደ ጣና ሐይቅ ገብተው መደበኛ ሥራቸውን ይጀምራሉ ነው ያሉት፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ አሊ ሰይድ (ዶክተር) ደግሞ ጢንዚዛዎቹ ከሜክሲኮ በመነሳት ዓለምን እየዞሩ የሚገኙ እና ለቪክቶሪያ ሐይቅ ህልውና ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከቱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ ለመታደግ ከወንጂ መተሃራ የመጡት ጢንዚዛዎችን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡

“የእምቦጭ ጉዳይ የፖለቲካና የጥቅም ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ የጢንዚዛ ገንዳዎችን ለማሠራት እስከ 30 ሚሊዮን ብር ተጠይቀናል” ሲሉም ወደ ሥራ ለመግባት እንደተፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡም ከከፍተኛ ተማራማሪዎች ጋር ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን ነው ዶክተር ዓሊ የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው

Previous articleከተማዋን ጽዱ አድርጎ እንግዶችን የመቀበል ተግባር በጎንደር ወጣቶች!
Next article“ልጆቼ ሆይ እንደታጨደው ሳር አትሁኑ! ገና እንደሚበቅለው እንደለመለመው ሁኑ እንጂ።” የጋሞ አባቶች