“መፎካከር ሳይኾን መመካከር ያስፈልገናል” ሐጂ ተዘራ አበበ

44

ባሕር ዳር: ጳጉሜ 06 /2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም የሕይዎታቸው ዓላማ ፤ የድርጅቶቻቸው አርማ እንደኾነ እድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ዘልቋል ይባላል፡፡ በዘመነ ደርግ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሆቴል ባለቤት እንደነበሩ ይነገራል። የሆቴላቸው መጠሪያ ሥም ደግሞ “ሰላም ሆቴል” ነበር፡፡ የሆቴል ድርጅታቸው ፈርሶ ወደ ሌላ የንግድ ሥራ ሲዘዋወሩ የንግድ ድርጅቱ ተቀየረ እንጂ ሥያሜው ግን ሰላምን ሳይለቅ “ሰላም የሞባይል ሴንተር” ተባለ፡፡

ከልጅነት እስከ ዕውቀት ካሳለፉባት ከተማቸው ባሕር ዳር እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረስ የዘለቀ የሰላም አምባሳደርነት ተሸላሚ ናቸው – ሐጂ ተዘራ አበበ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቆመው የሚያሳንጹ፣ መስጂድ ሲሠራ ያላቸውን ሁሉ የሚደግፉ ፤ በትምህርት ቤት ግንባታ የኀብረተሰብ ተሳትፎ ውስጥ ባለውለታ እና ባሕር ዳር የባለሃብቶቿን ድጋፍ በፈለገች ወቅት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው ይሏቸዋል፡፡

በአራት መንግሥታት እድሜ ውስጥ የሽምግልና አበርክቷቸው ጉልህ ነበር የሚባልላቸው ሐጂ “ሽምግልና መቀመጥ የጀመርኩት ገና 20 ዓመት ሳይሞላኝ ነበር” ብለውናል፡፡ ሲራራ ነጋዴ የነበሩት ሐጂ ተዘራ ከአስመራ እስከ አሰብ ለንግድ ሲመላለሱ ያጋጠሟቸው የሕይዎት ዘመን ፈተናዎች ሰላም የሕይወታቸው መርህ እንዲኾን እንዳስገደዳቸው ነግረውናል፡፡ የሰላም አስፈላጊነት የሚገባን ሰላም በራቀን እና ግጭት ባሳቀቀን ወቅት ነው ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሀገር ብትኾንም ጸጋዎቿን ዐውቀን በመጠቀም በኩል ለበርካታ ዘመን ውስንነቶች ነበሩብን ነው የሚሉት፡፡ ሳንሠራ ባሳለፍናቸው ዘመናት ሁሉ የከፋ የርሃብ እና ድርቅ ዘመናትን አሳልፈናል የሚሉት የሰላም አምባሳደሩ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን የሚፈቱት በሰከነ መንገድ መኾን እንዳለበት ካለፈ ታሪካችን መማር ይገባል ይላሉ፡፡ በሰው ልጅ እኩልነት ማመን እና ለመደማመጥ እድል መስጠት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ድህነትን ያክል ጠላት እና ኋላቀርነትን ያክል እንቅፋት ያለብን ሕዝቦች ነን የሚሉት ሐጂ ተዘራ ለዘመናት ከተጣባን ችግር ለመላቀቅ “መፎካከር ሳይኾን መመካከር ያስፈልገናል” ይላሉ፡፡

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የሚያውቁት የሽምግልና ሥርዓት እየተዳከመ መምጣቱ አሁን ለሚስተዋለው ግጭት መበራከት ምክንያት እንደኾነም ያምናሉ፡፡ ወደ ቀደመ ታላቅነታችን መመለስ እና ታላላቆችን ማዳመጥ ሕዝብ እና መንግሥት እንደገና ሊላበሱት የሚገባ ግብረ ገብነትም ነው ብለውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲሱ ዓመት የልዩነትን አጥር አፍርሰን የአንድነት ሐውልት ለመትከል የምንተጋበት ዘመን ይሆናል ” አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር
Next articleኽምጠ ዊከ ጋዜጠ ኻምል 15/2015 ዓ.ስ